በደቡብ ክልል በግጭት ተሳትፎ አድርገዋል የተባሉ 1 ሺህ 300 ተጠርጣሪዎች ምርመራ እየተደረገባቸው ነው

105
ሀዋሳ ሰኔ 16/2010 በደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በቅርቡ ተከስቶ በነበረው ግጭት ተሳትፎ አድርገዋል የተባሉ 1 ሺህ 300 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን የደቡብ ክልል ፖሊስ  ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ ግጭቱ የበለጠ ጉዳት እንዳያደርስ በየአካባቢው ያሉ የሕብረተሰብ ክፍልሎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡ የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍስሃ ጋረደው ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ግጭቱ ተከስቶባቸው የነበሩ የክልሉ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት ተረጋግተው አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል፡፡ ግጭቱ በሰላምና በፍቅር ተከባብሮ የሚኖሩ የክልሉን ህዝቦች እሴት የማይገልጽና እኩይ ተግባር ለመፈጸም በተዘጋጁ የተደራጁ ኃይሎች ቀስቃሽነት የተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ኮሚሽነር ፍስሃ እንዳሉት በሃዋሳ ከተማ፣ በሃዋሳ ዙሪያ ወረዳ ሻመና፣ በውልቂጤና ሶዶ ከተሞች በተፈጠረው ግጭት የ27 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ከ300 በላይ ዜጎች ላይ ከባድና ቀላል የአካላ ጉዳት ደርሷል፡፡ በተጨማሪም ግጭቱ በተከሰተባቸው የክልሉ አካባቢዎች 1ሺህ የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶችና የግል ድርጅቶች ቃጠሎ የደረሰባቸው ሲሆን በአብዛኞቹ ላይ ዘረፋ ተከናውኗል፡፡ በርካታ የመንግስትና የግል ተሽከርካሪዎች ላይም የቃጠሎ አደጋ መድረሱን የገለጹት ኮሚሽነር ፍሰሀ በሃዋሳ ከተማ በተከሰተው ግጭት በርካታ ዜጎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ በጌዲኦ ዞን ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ድንበር አካባቢ ባለፉት ሦስት ወራት የተፈጠረው አለመረጋጋት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል፡፡ ችግሩን በእርቅ ለመፍታት የተሞከረ ቢሆንም ለረዥም ዓመታት በፍቅር የኖረውን የሁለቱን ክልል ህዝብ ሰላም በማይፈልግ የተደራጃ ኃይል እየተመራ ዳግም ግጭት ማገርሸቱን ገልጸዋል፡፡ "በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የተፈፀመው ድርጊት የፖለቲካ ጥቅማቸውን ለማሳካትና የህዝቡን አብሮ የመኖር እሴት ለማጠልሸት በተደራጁ አካላት የተፈጸመ በመሆኑ ለአደጋው ድርሻ የነበራቸው አካላት በህግ ይጠያቃሉ" ብለዋል፡፡ በዚህም ግጭቱ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች 1ሺ 300 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ " የተዘረፉ ንብረቶችን መያዝ፣ በግጭቱ በመሳተፍም ሆነ ከበስተኋላ ሆነው ሲመሩ የነበሩ ተዋናዮችን፣ የመንግስት አካላትና ግለሰቦችን የመለየት ሥራ በመጀመሩ ምርመራው ሲጠናቀቅ ለህዝብ ይፋ ይሆናል" ብለዋል፡፡ በየአካባዎቹ ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለማብረድና ለይቶ ለማጥቃት የተሞከረውን ሙከራ በመከላከል በኩል ህብረተሰቡ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደነበር ኮሚሽነሩ ገልጸው፣ "ህዝቡ ባይሳተፍ ኑሮ ጉዳቱን የበለጠ የከፋ ያደርገው ነበር" ብለዋል፡፡ ህዝቡ እስካሁን በኃላፊነት ሲያደርገው የነበረውን ትብብር አጠናክሮ በመቀጠል በእኩይ ተግባሩ የተሳተፉትን ለመለየት በሚደረገው ጥረትም ተገቢውን መረጃና ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በርካታ የተዘረፉ ንብረቶች በግለሰቦች ቤት መሆናቸውን መረጃው አለን ያሉት ኮሚሽነሩ በህዝቡ ትብብርና በጸጥታ ኃይሉ የተቀናጀ ሥራ ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትን የማጋለጥ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል  ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም