የረጅም ጊዜ ብድር በማመቻቸት አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን ለማስገባት እየተሰራ ነው … ኮማንደር አህመድ መሐመድ

61

ኢዜአ፤ ታህሳስ 17/2012 በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የላዳ ባለንብረቶች ጋር በመነጋገር በዝቅተኛ ወለድ የረጅም ጊዜ ብድር አመቻችቶ አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን ለማስገባት  እየተሰራ መሆኑን የከተማ መስተዳድሩ የትራንስፖርት ባለስልጣን  አስታውቋል።

የትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮማንደር አህመድ መሐመድ እንዳሉት፤  አሮጌ ላዳዎችን በአዳዲስ ተሽከርካሪዎች የመቀየር ስራው የከተማዋን ገፅታ ከመቀየር ና የተገልጋዩን ምቾት ከመጠበቅ ባሻገር ለቱሪዝም መስህብነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል።

መቀየር አለባቸው ተብለው ተመዝግበው የሚገኙ ያገለገሉ ላዳ ታክሲዎች ምን ያህል ቁጥር እንዳላቸው የማጣራት ስራ መጠናቀቁን የጠቀሱት ኮማንደር አህመድ፤ ለጊዜው 8 ሺህ 95  ላዳዎች የተመዘገቡ ሲሆን አዳዲሶቹን በአንድ ግዜ ማስገባት ስለማይቻል በተለያየ ግዜ ወደ ሀገር  ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል ነው ያሉት።

አሮጌ ላዳዎቹን የመቀየር ስራ በአጭር ጊዜ እንደሚጀመር ገልጸው፤ ከናፍጣ በሚወጣው ጭስ የሚፈጠረውን የከተማዋን የአየር ብክለት ለመቀነስ አዳዲስ የሚገቡት በኤሌክትሪክ እንዲሰሩ ለማድረግ  እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

የብድር አገልግሎቱን ለማመቻቸት ከፋይናንስ ተቋማት ጋር እየተነጋገርን ነው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ግዢውን መንግስት እንዲፈጽም እየተሰራ ነው ብለዋል።

ያረጁ ላዳዎች የአወጋገድ ስርአት የሚከናወነው የቻለና አቅም ያለው በራሱ እንዲቀይር አቅም የሌለው ደግሞ መንግስት ተረክቦት ግምት የሚሰጠው እንደሆነም ተገልጿል።

አዳዲስ የሚገቡት ታክሲዎች  ከአየር ብክለት የፀዱና  ለከተማዋ በሚመጥን ደረጃ ያላቸው እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተጠቅሷል።

ላዳዎቹ ሞተራቸው ከማርጀቱ የተነሳ ለአየር ብክለት የሚያጋልጡ በመሆናቸው እንደ አስፈላጊነቱ ማቅለጫ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉም ኮማንደር አህመድ ገልጸዋል።

ከባንኮች ጋር በመነጋገር የላዳ ባለንብረቶች ዝቅተኛ ገንዘብ አስይዘው ያገኙትን እንዲቆጥቡና ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ በአነስተኛ የወለድ መጠን በብድር መልክ በባንኩ እንደሚሸፈንም ነው የጠቆሙት።

ባለንብረቶቹም  የተወሰነ እየቆጠቡ ክፍያውን መክፈል እንደሚኖርባቸው መግባባት ላይ  መደረሱን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስኪያጁ ፤  አዲስ የሚገቡት ታክሲዎች  እስካሁን ውሳኔ ላይ የተደረሰ ባይኖርም  ከአራት እስከ ሰባት ሰዎችን የሚይዙ ሊሆን ይችላል ነው ያሉት።

በአዲስ አበባ ከተማ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ላዳዎችን ከስራ በማስወጣት ከተማዋን በሚመጥን መልኩ በአዳዲስና ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች ለመተካት ከተማ አስተዳደሩ ከባለንብረቶች ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ገልጸው ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም