ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለፉት አምስት ወራት ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ አስገኘ

113

ኢዜአ፤ ታህሳስ 17/2012 ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለፉት አምስት ወራት ወደ ተለያዩ የውጭ ሃገራት ከላካቸው ምርቶች ከሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማስገኘቱን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ መኮነን ለኢዜአ እንደገለጹት በፓርኩ ውስጥ የተገነቡት ዘጠኝ ሼዶች በሙሉ ለስድስት የውጭ ባለሃብቶች ተላልፈዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥም አራቱ ምርቶታቸውን ወደ ተለያዩ የውጭ ሀገራት መላክ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

የሁለቱ ባለሃብቶች ኩባንያዎችም ማምረት መጀመራቸውንና በቅርቡ ምርታቸውን ወደ ውጭ ለመላክ በሂደት ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

ሌሎች ባለሃብቶችም ሸዶች እንዲሰጧቸው፤ ፖርኩ ውስጥ ስራ የጀመሩት ደግሞ ማስፋፊያ እንዲደረግላቸው እየጠየቁ መሆኑን አስታውቀዋል።

ወደ ማምረት የገቡት ባለሃብቶችም ሙሉ የወንድ ሱፍ፣ የስፖርት ትጥቅ፣ የሴት ፖርሳዎችን፣ ክርና ሌሎች አልባሳትን የጥራት ደረጃውን አሟልተው በማምረት ወደ ውጭ መላካቸውን ገልፀዋል።

ባለፉት አምስት ወራት ባለሃብቶች ወደ ውጭ ከላኩት ምርት ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር በላይ የዉጭ ምንዛሬ ለሃገሪቱ ማስገኘቱን አመልክተዋል።

ፓርኩ በአሁኑ ወቅት ለ2 ሺህ 84 ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።

''ፓርኩ በተያዘለት እቅድ መሰረት ተግባራቱን እያከናወነ ባለበት በዚህ ወቅት ሰሞኑን አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ''ፓርኩ ሊዘጋ ይችላል'' በሚል የተናፈሰው ወሬ እውነታውን ያልተረዳና በመረጃም ያልተደገፈ ነው'' ብለዋል።

እንደ አቶ ሙሉጌታ ገለጻ በጥቅምት ወር 2012 በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ያሉበት ሁኔታ በአዲስ አበባ  ሲገመገመ ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተመራጭ፣ በእድገት ላይ ያለና ግንባር ቀድም ሆኖ መገኘቱንም አስታውሰዋል።

በፓርኩ ስራ ከጀመሩት ባለሃብቶች መካከልም ትራይባስ የወንዶች ሙሉ ሱፍ አምራች ድርጅት ስራ አስኪያጅ ሚስ ሱን ችንጇን በሰጡት አስተያየት በፓርኩ ያለውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው በየወሩ ሁለት ኮንቴነር ሱፍ እየላኩ ከ30 ሺህ ዶላር በላይ የዉጭ ምንዛሬ እያስገኙ መሆናቸውነ ጠቅሰዋል።

ለ500 ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ያለምንም ችግር ተግባብተው እየሰሩ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ምርታቸው በውጭ ተፈላጊ በመሆኑ በብዛት ለማምረት ተጨማሪ ሸድ መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡

በትራይባስ ድርጅት ተቀጥሮ እየሰራ ያለው ወጣት አለልኝ መንበረ በበኩሉ በወር አራት ሺህ ብር እየተከፈለው በመስራት ራሱን እያስተዳደር እንደሚገኝ ተናግሯል።

''በድርጅቱ ተቀጥሬ በስምምነትና በፍቅር እየሰራሁ ከቤተሰብ ጥገኝነት ተላቅቂያለሁ'' ብሏል፡፡

የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለፈው ዓመት ወደ ውጭ ከላካቸው ምርቶች 5 ሚሊዮን ዶላር  የውጭ ምንዛሪ ያስገኘ ሲሆን በተያዘው የበጀት ዓመት ደግሞ 17 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዶ እየሰራ መሆኑ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም