የተቋቋመው አብይ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ መፍትሔ እስኪሰጥ ህብረተሰቡ ተረጋግቶ እንዲጠብቅ ጥሪ ቀረበ

87
ኢዜአ ታህሳስ 16/2012 የተቋቋመው አብይ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ መፍትሔ እስኪሰጥ ህብረተሰቡ ተረጋግቶ እንዲጠብቅ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጥሪ አቀረበ። የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥቷል። በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ መነሻው ባልታወቀ ምክንያት በመስጊዶችና በንግድ ተቋማት ላይ  ቃጠሎና ዘረፋ መካሄዱ ይታወሳል።   የኢትዮጵያ እስልም ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የችግሩን ምክያትና ጉዳት መጠን የሚያጣራ ኮሚቴ ማዋቀሩን ትናንት በሰጠው መግለጫ አስታውቆ ነበር። የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የተቋቋመው ኮሚቴ መልስ እስከሚሰጥ ህዝቡ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲጠብቅና ወደ ግጭት እንዳይገባ ገልጸዋል። ችግሮችን ለማለፍና ለመፍታት መቻቻል ቁልፍ መፍትሔ እንደሆነ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ ተወካይ ሼህ ቃሲም ታጁዲን በበኩላቸው ህዝቡ በመቻቻልና አንዱ የአንዱን ሃይማኖት በማክበር እንዲኖርና ከተለያዩ አካላት የግጭት መልዕክት እንዲቆጠቡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጨው የሰልፍ ጥሪ ማንንም የማይወክል በመሆኑ ህዝቡ ሰልፍ ከመውጣት እንዲቆጠብም አሳስበዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም