በጂንካ ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የመማር ማስተማሩ ስራ እንደቀጠለ ነው

71

ኢዜአ ታህሳስ 16/2012 ተማሪዎች ለመጡበት ዓላማ ብቻ እንዲተጉ በተደረገው ጥረት ሰላማዊ የመማር ማስተማሩ ስራ ማስቀጠል መቻሉን የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ።

የዩኒቨርሲቲው  ፕሬዚዳንት ፕሮፈሰር ገብሬ ይንቲሶ ለኢዜአ እንዳሉት  ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ በደባል አጀንዳ እንዳይታለሉ ከተቋሙና አካባቢው ማህበረሰብ ጋር አስቀድመው መወያየታቸው መልካም መሠረት መጣል ተችሏል።

"ለተማሪዎች የሚያስፈልጉ ጉዳዮችን በቅርበት በመከታተል ሟሟላት ከመቻላችንም በላይ በተቋሙ  ማህበረሰብና ተማሪዎች መካከል ቤተሰባዊ ግንኙነት እንዲኖር መደረጉ የመማር ማስተማር ሥራችንን ሰላማዊ አድርጎታል " ብለዋል፡፡

ከአዲስ ገቢ ተማሪዎችን ከማህበረሰቡ ጋር  በማስተዋወቅ  45 የከተማ ነዋሪዎች ተማሪዎችን በመቀበል የወላጅነት ሚና መጫወታቸውን ፕሮፈሰር ገብሬ  ጠቅሰዋል።

ተማሪዎች ለመጡበት ዓላማ ብቻ እንዲተጉ በተደረገው ጥረት የዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማሩ ስራ በተሳካ ሁኔታ ማስቀጠል እንደተቻለ ተመልክቷል።

በዩኒቨርሲቲው የሶስተኛ ዓመት የማኔጅመንት ተማሪ ታደለ ይሁን በሰጠው አስተያየት በተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ተፈጥሮ የነበረው ሁከት ተከትሎ  የመማር ማስተማር ስራ መስተጓጎል ተማሪዎችን መጉዳቱን ተናግሯል።

"የዚህ ችግር ዋናው ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ ደባል አጀንዳ ማስተናገዳቸው ነው" ሲል ጠቅሷል።

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢዉን ማህበረሰብ በማሳተፍ ከተማሪ አቀባበል ጀምሮ መልካም ግንኙነት በመፍጠሩ ያለምንም ችግር ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግሯል።

"ዓላማችን የሚሳካው የመማር ማስተማር ሥራ ሰላማዊ ሲሆን ብቻ ነው" ያለው ተማሪ ታደለ ለሰላም መጠበቅ የድርሻውን እንደሚወጠም ገልጿል፡፡

"የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኢትዮጵያ መገለጫ እንደመሆናቸው ከሁሉም የሀገራችን ክፍሎች በአንድ ግቢ መኖራችን ትልቅ ፍቅር ነው" ያለችው ደግሞ ተማሪ ተስፋነሽ ኢያሱ ናት፡፡

በተለይ በጂንካ አከባቢ ያሉ  የህብረተሰብ ክፍሎች   የሚያሳዩዋቸው ፍቅር ከቤተሰብ የማይተናነስ በመሆኑ ደስ መሰኘቷንም ጠቁማለች፡፡

ከመጡበት ዓላማ ውጪ በደባል አጀንዳዎች ግፊት የመማር ማስተማር ሥራን በሚያውኩ ተማሪዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም አመልክታለች፡፡

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የማስተማር ስራወን የጀመረው በ2010 ዓ.ም እንደሆነና በስሩ አራት  ኮሌጆችና 14 የትምህርት ክፍሎች በመምራት  ከ4ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ እንደሚገኝ ተቋሙ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም