የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ ይካሄዳሉ
ኢዜአ ታህሳስ 16 ቀን 2012 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ስታዲዮም ይካሄዳሉ።
የሊጉ ጨዋታ በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት እየተካሄደ ይገኛል።
የፊታችን ቅዳሜ ታህሳስ 18 ቀን 2012 ዓ.ም ከቀኑ በ9፡00 ሰዓት ወላይታ ድቻ ከወልቂጤ ከተማ፣ ስሁል ሽረ ከአዳማ ከተማ፣ ጅማ አባ ጅፋር ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሀዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታቸውን ያካሂዳሉ።
በተመሳሳይ ሰዓት ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕና ከባህርዳር ከተማ በክልል ስታዲዮም የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው።
መቐለ ሰብአ እንደርታ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ደግሞ እሁድ ታህሳስ 19 ቀን 2012 ዓ.ም ከቀኑ 9:00 ሰዓት በመቐለ ስታዲዮም ይገጥማሉ።
በአዲስ አበባ ስታዲዮም ደግሞ ሰበታ ከተማ ከፋሲል ከነማ ከቀኑ 9:00 ሰዓት የሚያደርጉት ጨዋታ የሳምንቱ ብቸኛ ጨዋታ ነው።
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ10 ነጥብ በሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።
ፋሲል ከነማ፣ ባህርዳር ከተማ፣ መቐለ ሰብአ እንደርታ እና ሀዋሳ ከተማ በእኩል 7 ነጥብ ከሁለት እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
ጅማ አባ ጅፋር፣ ድሬዳዋ ከተማና ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ 14 እስከ 16 ደረጃን ይዘው በሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጠዋል።
ፕሪሚየር ሊጉ ከተጀመረ አንስቶ በተደረጉ 32 ጨዋታዎች 67 ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን 103 ቢጫ ካርድ እና 5 ቀይ ካርዶች ታይተዋል።
የኮከብ ግብ አግቢነቱን የኢትዮጵያ ቡናው እንዳለ ደባልቄ እና የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም በ4 ጎሎች እየመሩ ይገኛል።