የጋራ መድረኩ አንድነታቸውን ለማጠናከር እንደረዳቸው የህብረተሰብ ወኪሎች ገለጹ

64

ኢዜአ ታህሳስ 16 ቀን 2012  የህዝብ ለህዝብ ውይይት መድረክ አንድነታቸውን ለማጠናከር የረዳቸው መሆኑን የኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የህብረተሰብ ወኪሎች ገለጹ።

የክልሎቹ የጋራ ውይይት መድረክ ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡

ከመድረኩ ተሳታዎች መካከል አቶ ኢብራሂም ሲራጅ በሰጡት አስተያየት የክልሎቹ ህዝቦች በደም፣ ቋንቋና ባህላዊ እሴቶች ተዋሃዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የህዝብ ለህዝብ ውይይት መድረኩም በመካከላቸው ያለውን ውህደትና አንድነት ለማጠናከር የሚያስችል መግባባትና መቀራረብ እንደፈጠረላቸው አመልክተዋል።

"ከድህነት የምንወጣት እድላችንም በጋራ ጥረታችን ይወሰናል፤ በዘላቂነት አብረን እንደምንቀጥልም አምናለሁ" ሲሉ ገልጸዋል።

ሠላምን ለማምጣት የሚያስፈልገው ፍቅር መሆኑን የገለጹት ደግሞ  አቶ ሃሰን ወርቁ የተባሉ ተሳታፊ ናቸው።

"በተከታታይ ባደረግናቸው ውይይቶች በፈጠርነው መቀራረብ እርስ በርስ የሚያጋጩንን ኃይሎች በመለየት ሰላማችንን ማስጠበቅ ችለናል" ብለዋል ።

ከአባቶቻቸው ያገኙትን የመቻቻልና የመከባበር ልምድ በማጎልበት አብሮነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

"መንግስት ህግን በማስከበር ረገድ የሚታዩበትን ችግሮች ማስተካከል አለበት" ያሉት ተሳታፊው  የህዝብና የሀገር አንድነትን ለማፍረስ የሚጥሩ አክቲቪስቶችንና መገናኛ ብዙሃንን ስርዓት እንዲያስይዝ ጠይቀዋል፡፡

አቶ አለማየሁ መልካሙ  የተባሉ ተሳታፊ በበኩላቸው "የልጆቻቻንን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር የጥፋት ኃይሎችን መንገድ መዝጋት አለብን" ብለዋል።

የህዝብ ለህዝብ መድረኮቹ የጋራ እሴቶቻቸውንና አንድነታቸውን ለማጠናከር  ጠቃሚ እንደሆኑም አመልክተዋል።

"በክልሎቹ የብሔርና ኃይማኖት ልዩነቶችን በማራገብ ሀገራዊ ለውጡ በህዝቦች እንዳይታገዝ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን መንግስት ችላ ሊል አይገባም" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሰናይት ቀነአ ናቸው።

እንደ ተሳታፊዎቹ ገለጻ በተከታታይ በተደረጉ ውይይቶች ችግሮቻቸውን በግልጽ በመለየትና መፍትሔ አስቀምጠው በመስራታቸው አንድነታቸውን ማጠናከር ችለዋል።

የአሶሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ኡመር አህመድ የክልሎቹ ህዝቦች አንድነትን በማጠናከር ረገድ ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለይም የጋራ ጠላት የሆነውን ድህነት ለማስወገድ ለተጀመረው ጥረት የዜጎችን በሠላም ወጥቶ የመግባት ጉዳይ ትኩረት እንደሚደረግበት  አስታውቀዋል፡፡

ሠላም ወዳድ የሆኑ የክልሎቹ ህዝቦች የሚያጋጥሙ ችግሮችን በይቅርባይነት እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲሻገሩ ከንቲባው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በጋራ ውይይት መድረኩ ከክልሎቹ የተውጣጡ ከ500 በላይ የህብረተሰብ ወኪሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም