መቀሌ ዩኒቨርሲቲ 7 ሺህ 350 ተማሪዎችን አስመረቀ

82
መቀሌ ሰኔ 16/2010 መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 7 ሺህ 350 ተማሪዎች አስመረቀ። ዩኒቨርሲቲው ለሴቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት አስታውቀዋል። ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 4 ሺህ 844 የሚሆኑት በመጀመሪያ ዲግሪ፣ 2 ሺህ 464ቱ ደግሞ በሁለተኛ  ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው። ዛሬ ለምረቃ ከበቁ ሰልጣኞች መካከል 41ዱ በአየር ንብረት ለውጥና በገጠር ልማት የትምህርት መርሃ ግብር በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቁ መሆናቸውንም ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህሕይወት አስታውቀዋል። ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል የሴቶችን አቅም ማሳደግ መሆኑንም ጠቁመው፣ በተደረገው እገዛ አንድ ሺህ 350 ሴት ተማሪዎች 3 ነጥብ 25 እና ከዚያ በላይ ውጤት ማስመዝገባቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል። ሴት መምህራን በተቋሙ በብዛት እንዲቀጠሩ መደረጉንና ሴት መምህራን በምርምር ሥራ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲጎለብት ለሴት ተመራማሪዎች ብቻ የሚሰጥ ገንዘብ መመደቡንም ፕሮፌሰር ክንደያ ገልጸዋል። እንደ ፕሮፌሰር ክንዳያ ገለጻ፣ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎትን ለማርካት ዩኒቨርሲቲው በመደበኛ፣ በተከታታይና በርቀት የትምህርት መርሃ ግብሮች 16 የሦስተኛ ዲግሪንና 257 የሁለተኛና የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት መርሃ ግብሮችን ከፍቶ በማስተማር ላይ ነው። በተጨማሪም 11 የልዩ ሙያ የምስክር ወረቀትና ሦስት የድህረ ምረቃ ዲፕሎማና ሰርተፍፊኬት መርሃ ግብሮችን ከፍቶ በማሰልጠን ላይ ይገኛል ። ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ባካሄደው የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ አትሌት ሻለቃ ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ የተለያዩ ታዋቂ ሰዎች፣ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የምሩቃን ቤተሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም