በድሬዳዋ ለቤተ-እምነቶች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሰጠ

99
ኢዜአ ታህሳስ 15/2012፡- በድሬዳዋ አስተዳደር ለ82 ቤተ-እምነቶች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሰጠ የድሬዳዋ አስተዳደር የይዞታ ማረጋገጫውን የሰጠው  ትላንት ለእስልምና ፣ ለኦርቶዶክስና  የፕሮቴስታንት ቤተ-እምነቶች ነው፡፡ የይዞታ ማረጋገጫውን  የሰጡት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃርና የድሬዳዋ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ደራራ ሁቃ ናቸው፡፡ አቶ ከድር ጁሃር በዚህ ወቅት ቤተ-እምነቶች  ለዓመታት ሲቀረቡ የቆዩት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የማግኘት ጥያቄ በትዕግስት በመጠበቃቸው አድንቀዋል፡፡ በድሬዳዋ የሚገኙ ቤተ-እምነቶች የጋራ ጥረትና ህብረት የተገነቡና የጋራ የይዞታ መገለጫዎች እንደሆኑም ጠቅሰዋል። ይህንን  ለመናድና ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማሳካት የሚሯሯጡ አካላትን በተቀናጀ መንገድ መከላከል እንደሚገባቸው አመልክተዋል። የድሬዳዋ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ደራራ ሁቃ " የኃይማኖት ተቋማት ለሰላም መከበርና ለህዝቦች መተባበር እያደረጉት ላለው ጥረት አመስግነዋል። ሀገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ጎዳና ዳር በማድረስ ረገድ የማይተካ ሚናቸውን እንዲያጠናክሩም አመልከተዋል፡፡ የድሬዳዋ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በመወከል የይዞታ ማረጋገጫውን የተቀበሉት ሐጂ አብደላ ሳኔ የሀገርና የድሬዳዋ ቅርስ የሆነው የጁማኣ መስጂድ የ80 ዓመታት ጥያቄ ጭምር ዛሬ መፍትሄ በማግኘቱ መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡ "አስተዳደሩ ላደረገልን መልካም ሥራ እናመሰግናለን "ብለዋል፡፡ ሊቀ-ብርሃናት ማትያስ በቀለ በኦርቶደክስ ቤተክርስቲያን የድሬዳዋ ሐገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ በበኩላቸው "ቤተ-እምነቶች በመተባበርና በመቀናጀት በሀገር የተጀመረውን ለውጥ  ዳር ለማድረስ ይሰራሉ " ሲሉ ገልጸዋል። በምሥራቅ ጎጃም ሞጣ ከተማም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ቤተ-እምነቶችን የሚያቃጥሉ የትኛውንም  ኃይማኖት እንደማይወክሉ አስታውቀዋል፡፡ የዘመናት  ጥያቄዎችን በህጋዊ መንገድ ምላሽ ማግኘታቸውን የተናገሩት ደግሞ የድሬዳዋ ወንጌላውያን አብያተ-ክርስቲያን ህብረት በመወከል ካርታውን የተቀበሉት ፓስተር ምስክር አበበ ናቸው፡፡ ሀገራችን የጀመረችው የከፍታ ጉዞ በሰመረ መንገድ ዳር እንዲደርስ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡ ለቤተ-እምነቶች የይዞታ ማረጋገጫ በተሰጠበት ስነሰርዓት የአስተዳደሩ አመራሮች እና የጠቅላይ ሚነስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሞሃ-ዘጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተገኝተዋል፡፡ በዚህ ወቅት ዲያቆን ዳንኤል ድሬዳዋ በሀገር አቀፍ ደረጃ የምትታወቅበትን ሰላምና ፍቅር ለመመለስ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲረባረቡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም