መንግስት ለመገናኛ ብዙሃን መረጃ የማቅረብ ክፍተቱን ለመፍታት ይሰራል ... ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

74
ኢዜአ፤ ታህሳስ 15/2012 መንግስት ለመገናኛ ብዙሃን መረጃ በማቅረብ ረገድ የሚታይበትን ችግር ለመፍታት እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገለጸ። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት ''የሚዲያ ሚና ሓሳቦችን በማቀራረብ'' በሚል ርዕስ የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሂዷል። በውይይቱ የከሰዓት መርሃ ግብር ማህበራዊ ሚዲያ ከነባሩ መገናኛ ብዙሃን አውታሮች ጋር ስላላቸው መስተጋብርና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል። በውይይቱ ላይ በርከት ያሉ ሃሳቦች የተሰነዘሩ ቢሆንም መንግስት ከነባሩ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ጋር ያለው ግንኙነት ወጥነት የሌለው መሆኑ ተመልክቷል። ለዚህ እንደ አመላካች ተደርጎ የቀረበው መደበኛ ሚዲያዎች ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ በፍጥነት ማቅረብ አለመቻላቸው ነው። በተጨማሪም መደበኛ አውታሮቹ በአግባቡ የመመራት ችግር ቢኖርባቸውም በዋናነት ትክክለኛውን መረጃ የማግኘት ችግር እንዳለባቸው በውይይቱ ተነስቷል። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ''በለውጡ ብዙ ማሻሻያዎች ቢደረጉም የሚቀሩ ነገሮች አሉ'' ብለዋል። በለውጥ ጉዞው መረጃን ተደራሽ ለማድረግ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ጀምሮ በቋሚነት መረጃ የመስጠት ጅምር መኖሩን ተናግረዋል። ከዚህ ጎን ለጎን ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን በማህበራዊ ትስስር ገጾች ጭምር ተደራሽ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋ:: ይህም ሆኖ በተለይ ችግሮች ሲያጋጥሙ ትክክለኛ መረጃ ከመስጠት አንጻር ከፍተኛ ክፍተት መኖሩን የጠቀሱት አቶ ንጉሱ፤ በቀጣይ የማሻሻል ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል። ከአዲሱ ሚዲያ መስፋፋት ጋር ተያይዞም የተሻሉ ዕድሎች ቢኖሩም ስጋቱም በዛው ልክ መጨመሩን ገልጸዋል። ሚዲያውም ሰላም፣ እርቅንና አብሮነትን ከመስበክ ይልቅ በአሉታዊ ጉዳዮች ተጠምዷል ተብሏል። ችግሩን ለመቆጣጠር በቅድሚያ ኃላፊነት የሚሰማቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በስፋት በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ተሳትፏቸው ሊያድግ እንደሚገባ ተመልክቷል። በውይይቱ ላይ በስፋት የተነሳው ማህበራዊ ሚዲያው ወጥነት ባለው መልኩ ክትትልና ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ ተገልጿል። በተቃራኒው ደግሞ ይህንኑ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት የሚሰራጨውን ሃሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን ለመገደብ የተዘጋጀው ረቂቅ ህግም ተነቅፏል። ረቂቅ ህጉ በቂ ውይይት ያልተደረገበትና መግባባት ያልተደረሰበት ከመሆኑም ባለፈ ሕጉ የጭቆና መሳሪያ በመሆን የግለሰቦችን መብት ሊያፍን እንደሚችል ተሰግቷል። የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊው አቶ ንጉሱ በማጠቃለያ ንግግራቸው መገናኛ ብዙሃን ከአሉታዊ ዘገባዎች ወጥተው ገንቢ ስራዎች ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ሚዲዎች የማስታረቅ፣ ሰላም የማምጣትና የማረጋጋት ድርሻቸው ትልቅ መሆኑን ተረድተው ትኩረታቸውን እንዲቀይሩ ጠይቀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም