የተደራጀ መረጃ ሳይኖር አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ማድረግ አዳጋች እንደሆነ ተገለጸ

51
ኢዜአ ታህሳስ  15 /2012 በትምህርት ላይ የሚገኙ አካል ጉዳተኞችን መጠን የሚያሳይ የተደራጀ መረጃ ሳይኖር አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ማድረግ አዳጋች እንደሆነ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሄራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ገለጸ። የከፍተኛ ትምህርት ከሚከታተሉ አካል ጉዳተኞች ውስጥ 22 በመቶ የሚሆኑት በአካባቢ ተደራሽነት ችግር ትምህርት ያቋርጣሉ ተብሏል። የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሄራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን አካል ጉዳተኞች በትምህርትና በጤና እንዲሁም በሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ መክሯል። የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በዚሁ ወቅት አንደገለጹት፤ አካል ጉዳተኞችን እንደ ማንኛውም ዜጋ ከዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል። አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግም የተደራጀ መረጃ ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል። በመሆኑም የአካል ጉዳተኞችን የትምህርት፣ የጤና እንዲሁም ሌሎች ጥቅል የሆኑ መረጃዎችን ማደራጀት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ የተደራጀ መረጃ ሳይኖር አካል ጉዳተኛውን ተጠቃሚነት ማድረግ ፈታኝ እንደሚሆን አመልክተዋል። ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ መሰረት እድሜያቸው ለትምህርት ከደረሰ አካል ጉዳተኞች መካከል የትምህርት ዕድል ማግኘት የቻሉት ከ7 ነጥብ 8 በመቶ ያልበለጡ ናቸው። ከነዚህ መካከል ለከፍተኛ ትምህርት የሚበቁ አካል ጉዳተኞች ውስጥ 22 በመቶ የሚሆኑት በተቋማት ምቹነት መጓደል የተነሳ ትምህርት ለማቋረጥ እንደሚገደዱ ተገልጿል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ዲን ዶክተር ደበበ ኤሮ በበኩላቸው፤ ''አካል ጉዳተኞችን ከሌሎች ዜጎች እኩል ተጠቃሚ  ለማድረግ በመጀመሪያ የአመለካከት ለውጥ በሁሉም ውስጥ ሊፈጠር ይገባል'' ብለዋል። በአገሪቷ የሚተገበሩት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች አካል ጉዳተኞችን ያማከለ መሆን እንደሚገባውም ገልጸዋል። በከፍተኛ  የትምህርት ተቋማት ውስጥ ለአካል ጉዳተኞች ተብሎ የተመቻቸ የተለየ መገልገያ አለመኖሩን ገልጸው፤ ''በዩኒቨርሲቲው ከሚገኙ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች መካከል አይነ ስውራንን ብቻ ብናይ በፈተና ጊዜ መፈተኛ ክፍል ስለማይኖራቸው ኮሪደር ላይ ነው የሚፈተኑት'' ብለዋል። አካል ጉዳተኞች በኢኮኖሚው ራሳቸውን ለመቻል በሚያደርጉት ጥረት የስራ እድል እንደሌሎች ዜጎች እኩል ተጠቃሚ ባለመሆናቸው በርካታ ችግሮችን እንደሚጋጡ የመድረኩ ተሳታፊዎች ገልጸዋል። አብዛኛው የህብረተሰብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርጎ የተሰራ ባለመሆኑ ይህም ሊታሰብበት እንደሚገባ ተወያዮቹ አንስተዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ገነት አባተ የጉዳዩን አሳሳቢነት ገልጸው በትኩረት እንዲሰራ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደረግ ገልጸዋል። አካል ጉዳተኞች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የአለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብት ጥበቃ ስምምነት ፈርማ ከ10 አመት በፊት መቀበሏን የሚታወቅ ሲሆን መንግስት ትክክለኛውን የአካል ጉዳተኞች ቁጥር ለማሳወቅ ቃል ገብቷል። በመድረኩ  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የጤና ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም