ውህደቱን በተሳሳተ መንገድ መነጋገሪያ የማድረጉ ጥረት ከግል ጥቅም የመነጨ ነው...አቶ አሻድሊ ሃሰን

125
አሶሳ (ኢዜአ) ታህሳስ 15 / 2012  ውህደቱን በተሳሳተ መንገድ መነጋገሪያ የማድረጉ ጥረት የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በሚፈልጉ ጥቂት ግለሰቦች ፍላጎት የመነጨ ነው" ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን አስታወቁ፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸው “የስምንት ክልሎች መንግስታትና ህዝቦች ውህደቱን አምነው ተቀብለው ሀገሪቱን ወደ ፊት እየወሰዷት ነው" ብለዋል ውህደቱ ህግና ስርዓትን ተከትሎ መፈጸሙን የገለፁት ርዕሰ  መስተዳድሩ ውህደቱ  ፈጽሞ ከአሃዳዊ ስርዓት ጋር የሚያገናኘው ነገር አለመኖሩን አስታውቀዋል። በፓርቲው አደረጃጀት ራስን በራስ በማስተዳደር ላይ የሚመጣ ለውጥ አለመኖሩን የክልሉ ህዝብም ሆነ ቤጉህዴፓ በግልጽ የተረዱት መሆኑን ገልጸዋል። ህገ-መንግስቱ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በግልጽ ቢያስቀምጥም ባለፉት 27 ዓመታት ተግባራዊ ባለመሆኑ የክልሉ ህዝብ ያጣቸው በርካታ ጥቅሞች መኖራቸውን አስታውሰዋል፡፡ የሌሎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ውህደት የጠቀሱት አቶ አሻድሊ " የእኛን መዋሃድ በተሳሳተ መንገድ የመነጋገሪያ አጀንዳ የማድረግ እንቅሰቃሴ ግለሰቦች የራሳቸውን ፍላጎት ለማስጠበቅ የሚያደርጉት ጥረት ነው" ብለዋል፡፡ ውህደቱ በእኔ ቡድን መሪነት ለምን አልተካሄደም በሚል አዘማሚያ ካልሆነ በቀር ፓርቲው ሃገሪቱን ካለችበት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግር ወደ ብልጽግና ሊያሸጋግራት የሚያስችል መሠረት እየጣለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “ሀገራችን ወደ ብልጽግና እንድትገባ እንፈልጋለን፤ ውህደቱን ያልተቀበሉ አካላት በቆይታ ሲገባቸው የሚመለሱበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል" ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡ ለውጡ ያሰፋውን የፖለቲካ ምህዳር ተጠቅሞ የተሻለ እቅድ ይዞ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ሀገሪቱን የሚመራበት ሁኔታ በመንግስት እየተመቻቸ እንደሆነም  አመልክተዋል፡፡ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሃገራዊም ሆነ ክልላዊ ፓርቲዎች ህግን ተከትለው እስከሰሩ ድረስ አብረው ከመስራት እንደማያግዳቸው አስታውቀዋል፡፡ ህብረተሰቡ ከተሳሳተ ፕሮፓጋንዳ ራሱን በመጠበቅ ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮችን በየደረጃው ከሚገኙ የመንግስት መዋቅሮች ጠይቆ በመረዳት ሰላሙን እንዲያረጋግጥም  ርዕሰ መስተዳድሩ  መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም