በትግራይ የድግስ ወጭ በማህበረሰብ አኗኗርና ኢኮኖሚ ፈጣን ለውጥ እንዳይመጣ ተጽእኖ መፍጠሩን በጥናት ተመለከተ

53
ኢዜአ ታህሳስ 15 /2012 በትግራይ ክልል የድግስ ወጭ በማህበረሰብ አኗኗርና ኢኮኖሚ ፈጣን ለውጥ እንዳይመጣ ተጽእኖ መፍጠሩን በዘርፉ የተካሄደ ጥናት አመለከተ። የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በዘርፉ ባካሄደው ጥናት ላይ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ ትላንት በአብይአዲ ከተማ አካሄዷል። በቢሮው  የኮሙዩኒኬሽንና የሚዲያ ባለሙያና የጥናቱ ቡድን አባል  አቶ ኃይለኪሮስ ካሕሳይ በክልሉ የድግስ ወጭ በማህበረሰብ አኗኗርና በኢኮኖሚ ላይ ስለሚኖረው አሉታዊ ተጽእኖ በመፈተሽ የመፍትሄ ሀሳብ ለማመላከት በቢሮው የተዘጋጀውን የዳሰሳ ጥናት አቅርበዋል ። ጥናቱ በክልሉ 10 ወረዳዎች ለሰርግ፣ ተስካር፣ ልደት፣ ክርስትና፣ለምርቃት ጨምሮ ለተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች በሚከናወኑ ድግሶች ወጭ ላይ የተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል። ባለሙያው ባቀረቡት የጥናት ፅሁፍ  በአንድ ወረዳ ብቻ ለድግሶች ማካሄጃ በአመት ከ44 እስከ 133 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ወጭ እንደሚሆን ተመልከቷል ። በክልሉ በድግስ የሚባክን ከፍተኛ ወጭ በግለሰብም ሆነ በማህበረሰብ አኗኗርና ኢኮኖሚ ፈጣን ለውጥ እንዳይመጣ የራሱ የሆነ ተጽእኖ ማሳደሩን በጥናቱ ተጠቁሟል። ድግስ ማህረሰብን በማቀራረብና ግንኙነትን በማጠናከር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ያመላከተው ጥናቱ ባንጻሩ ''ከማን አንሼ'' በሚል ባህላዊ ፈሊጥ የሚከወን አቅምን ያላገናዘበና  ከመጠን ያለፈ ድግስ የሚያስከትለው የኑሮና የኢኮኖሚ ጫና ከፍተኛ መሆኑ ተመልቷል። ከመጠን ባለፈ ድግስ የሚባክን ከፍተኛና አላስፈላጊ ወጭ ለመቀነስ በማህበረሰብ ውስጥ ተሰሚነት ያላቸው የሀይማኖት አባቶችና መሪዎች ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑ በጥናቱ ተጠቁሟል ። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሀዱሽ ካሱ ከልክ በላይ ለድግስ ወጪ ማድረግ ለኢኮኖሚ እድገት እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል። በአንዳንድ ወረዳዎች በሃይማኖት አባቶች የተጀመረው የወጪ ገደብ ማስቀመጥ ስራ ሊጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል። የቁጠባ ባህል ለማጎልበት የተጀመሩ አደረጃጀቶችን የማጠናከርና የተሞክሮ ልውውጥ ስራዎችን ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተዋል። የክልሉ መንግስት በዘርፍ እየተስተዋለ ያለውን ብክነት ለማስቀረት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠትና ከባለድርሻዎች ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራ አቶ ሐዱሽ አስታውቀዋል ። የትግራይ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተወካይ አባ ጥዑም በርሀ "የፍሰስ ተፋስስ ድግስ በሃይማኖት አይፈቀድም" ብለዋል። "ለማህበራዊ ድግሶች የሚባክን ወጪ ለመቀነስና የቁጠባ ባህልን ለማጎልበት እንሰራለን" ብለዋል። እንደ ተወካዩ ገለጻ በመንግስት በኩልም አሰራርና መመሪያ ከማውጣት ጀምሮ በዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል። የአላማጣ ከተማ እስልምና ጉዳይ ተወካይ አቶ ኑሩሁሴን ኢብራሂም ለሰደቃም ሆነ ለሰርግ ከልክ በላይ መደገስ ሃይማኖቱ እንደማይፈቅድ ተናግረዋል። "የሃይማኖት መሪዎች አርአያ በመሆን ከሰራንና ከመራን ችግሩን መከላከል እንችላለን" ያሉት አቶ ኑሩሁሴን በከተማው በዘርፉ የሚወጣ ብክነትን ተቋማቸው ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል። በከተማው የሙስሊም ማህበረሰብ ዘንድ ለተለያዩ ዝግጅቶች የሚባክን ሀብትን ለመከላከል አሰራርና ደንብ ወጥቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። እንደየ ድግስ ዝግጅት አይነቱ ከተቀመጠው ገደብ  በላይ ወጪ ያደረገ ግለሰብ ወይም አካል ከ5 እስከ 7 ሺህ ብር እንዲቀጣ በማህበረሰቡ መተዳደሪያ ደንብ መደንገጉን ለአብነት ጠቅሰዋል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም