በፍንዳታው ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች አስቸኳይ የህክምና እርዳታ እያገኙ ነው

67
አዲስ አበባ ሰኔ 16/2010 በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ላይ በደረሰው የቦንብ ፍንዳታ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች አስቸኳይ የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ  ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ላመጧቸው ለውጦች ድጋፍና እውቅና መስጠትን ዓላማ ያደረገው የድጋፍ ሰልፍ ዛሬ ተካሂዷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰልፉ ላይ በመገኘት ለድጋፉ ሰልፉ ታዳሚዎች መልእክተ ካስተላለፉ ከደቂቃዎች በኋላም የቦምብ ፍንዳታ ተከስቷል። ፍንዳታውን ተከትሎ በርካታ የፖሊስ አባላት ወደ ስፍራው በማምራት የተፈጠረውን ክስተት በማረጋጋት ላይ መሆናቸውንም ቀደም ሲል ባወጣነው ዘገባ ገልጸናል። በተጨማሪም አምቡላንሶች ወደ ስፍራው በማቅናት የተጎዱትን ሰዎች ወደ ዘውዲቱና የካቲት 12 ሆስፒታሎች በመውሰድ የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው። በዘውዲቱ ሆስፒታል ዶክተር የኔአለም እንደገለጹት፤ በድጋፍ ሰልፉ ላይ በተከሰተው ፍንዳታ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው 23 ዜጎች  በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታሉ ደርሰው ሕክምና እየተከታተሉ ናቸው። የሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያዎችም "ፈጣን እርዳታ እያደረጉላቸው ይገኛሉ" ብለዋል። የካቲት 12 ሆስፒታል ህክምና ስፔሻሊስትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል አበበ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት፤ ፍንዳታው ከተከሰተበት ሰዓት አንስቶ ወደ ሆስፒታሉ 56 ተጎጂዎች በአምቡላንስ መጥተዋል። በፍንዳታው የተጎዳ አንድ ሰውም ባጋጠመው ከባድ የጭንቅላት ጉዳት ወደ አለርት ሆስፒታል ሪፈር እንዲላክ መደረጉንም አክለዋል። በአሁኑ ወቅትም ወደ ሆስፒታሉ የገቡ ተጎጂዎች አስፈላጊውን የህክምና እርዳታ እያገኙ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት። በአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ ከሰዓት በኋላ ለኢቲቪ በሰጡት መረጃ መሰረት በድጋፍ ሰልፉ ላይ በደረሰው ጥቃት የተጎዱ ዜጎች 100 ያህለ ይሆናሉ። ከነዚህ መካከል 15ቱ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። አደጋውን ያደረሱ አካላትን በቁጥጥር ስር ለማዋልም የጸጥታ አካላት በተጠናከረ መልኩ ስራዎችን መጀመራቸውን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ ህዝቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን "ወንጀለኞችን የማጋለጥ ተግባሩን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል" ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። የጸጥታ ኃይሉ የሚያደርሰውን መረጃና ተጎጂዎች ያሉበትን ደረጃ በሚመለከት ኢዜአ መረጃዎችን እየተከታተለ በወቅቱ የሚያደርስ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም