የግል ድርጅቶች ለጡረታ አበል ከሰራተኞቻቸው የሚሰበስቡትን ገንዘብ በወቅቱ ገቢ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል

66

ኢዜአ ታህሳስ 15/ 2012 የግል ድርጅቶች ከሰራተኞቻቸው ለጡረታ አበል የሰበሰቡትና በወቅቱ ገቢ ያላደረጉት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ የጡረታ መዋጮ በህግ ተጠያቂ በማድረግ ገቢ እንዲሆን ማድረጉን የፌደራል የግል ድርጅቶች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ።

በኤጀንሲው የሰሜን ሪጅን ጽህፈት ቤት በጡረታ አበል አሰባሰብ ላይ በሚታዩ ክፍተቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ትናንት በመቀሌ ከተማ አካሂዷል።

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የፌዴራል የግል ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የህግ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ግርማ ሲሳይ እንዳሉት በአገሪቱ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰራተኞችን የሚያንቀሳቅሱ ከ130 ሺህ በላይ የግል ተቋማት ይገኛሉ።

በተቋማቱ ስር ያሉ ኣብዛኞዎቹ ሰራተኞች ከሚያገኙት ገቢ  የጡረታ አበል ቢከፍሉም አሰሪዎቻቸው ገንዘቡን ለኤጀንሲው በወቅቱ ገቢ እንደማያደርጉ አስታውሰዋል።

በአገሪቱ ከሚገኙ ከ130 ሺህ የግል ተቋማት መካከል ከ9 ሺህ በላይ ድርጅቶች ከሰራተኞቻቸው ለጡረታ አበል ብለው የሰበሰቡትን ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በወቅቱ ወደ ኤጀንሲው ገቢ ሳያደርጉ መቆታቸውን በተደረገው የኦዲት ቁጥጥር ስራ መረጋገጡን ገልጸዋል።

ድርጅቶቹን በህግ ተጠያቂ በማድረግና በማስወሰን የሚፈለግባቸውን ገንዘብ ከባንክ ሂሳባቸው ተቀንሶ ወደ ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲው ገቢ እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በግል ተቋማት ውስጥ ያሉ ሰራተኞች የጡረታ አበላቸው እንዲከበር የግል ድርጅቶች የሰበሰቡትን ገንዘብ በወቅቱ ለሚመለከተው አካል ገቢ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በትግራይ ክልል የሚገኙ የግል ተቋማት ከሰራተኞቻቸው የሰበሰቡትን ገንዘብ በወቅቱ ለሚመለከተው ኤጀንሲ ገቢ በማድረግ በምሳሌነት እንደሚጠቀሱ ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም ክልሉ ባለፈው ዓመት ባከናወነው የላቀ ተግባር የማበረታቻ የዋንጫ ሽልማት ተሸላሚ እንደነበር ተናግረዋል።

በኤጀንሲው የሰሜን ሪጅን ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ገብረኪዳን ሓዱሽ በበኩላቸው በትግራይ ክልል ከ20 ሺህ በላይ የግል ተቋማት ይገኛሉ።

ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የግል ተቋማቱ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ የጡረታ አበል ከሰራተኞቻቸው ሰብስበው በወቅቱ ወደ ሪጅን ጽህፈት ቤቱ ገቢ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

በክልሉ ውስጥ እስካሁን ድረስ የተመዘገበው ውጤትም አፈፃፀሙ ከእቅድ በላይ መሆኑን ነው አቶ ገብረኪዳን ያመለከቱት።

የተቀናጀ ስራ በማከናወን ፤ የጡረታ መዋጮ በመሰብሰብና ከ600 ለሚበልጡ የግል ሰራተኞች በወቅቱ የጡረታ አበል በመክፈል አርአያነት ያለው ተግባር መከናወኑም አስታውቀዋል፡፡

በቀጣይም የግል ተቋማትና ሰራተኞቻቸው በቅንጅት በመስራት ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ከተሳተፉ ሰራተኞች መካከል የኒኮላስ አካዳሚ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ገሰሰ እንዳሉት ከምናገኘው ገቢ የጡረታ መዋጮ መክፈላችን ነገን በማሰብ በመሆኑ ለተግባራዊቱ በንቃት ልንሳተፍ ይገባል ብለዋል።

የካዛ ካፒታል የግል ተቋም የሰው ሃይል ልማት አስተባበሪ ወይዘሮ ለተብርሃን በየነ በበኩላቸው እያንዳንዱ ሰራተኛና አሰሪ መብቱና ግዴታውን በወቅቱ ከተወጣ በስራ ላይ መነቃቃትን ይፈጥራል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም