ክልሎችና የድሬደዋ አስተዳደር በመስቀል አደባባይ በተፈጸመው ጥቃት የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ሃዘናቸውን ገለጹ

70
አዲስ አበባ ሰኔ16/2010 በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የእውቅናና ምስጋና ሰልፍ ላይ በተፈጸመ የቦንብ ጥቃት በደረሰው ጉዳት ክልሎችና የድሬደዋ አስተዳደር የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገለጹ። ዛሬ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የ'መደመር ቀን' በሚል ዜጎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያላቸውን አድናቆትና ምስጋና አቅርበዋል። በዚህ ወቅት በእኩይ ሃይሎች የቦንብ ጥቃት ተፈጽሞ በሰልፉ ላይ ከሚተሳተፉ ዜጎች መካከል ጥቂት ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፤ የሰው ህይወትም አልፏል። ይህን የደረሰውን ጉዳት በማስመልከት የአማራ፣ የትግራይና የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግስታት እና ህዝቦች የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል፡፡ በመንግስት የተጀመረውን ለውጥ ለመደገፍ እና ለማመስገን በተዘጋጀው የድጋፍ ሰልፍ በደረሰው ጉዳት እና የሰው ህይወት ማለፍ የሶስቱ ብሄራዊ ክልሎች መንግስታት እና ህዝቦች የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልፀዋል፡፡ ለተጎጂ ቤተሰቦችና ለመላ ኢትዮጵያዊያንም መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡ ይህንን እኩይ ተግባርም የክልሎቹ መንግስታት እና ህዝቦች በጽኑ እንደሚያወግዙ የሶስቱ ክልሎች ኮሙንኬሽን ጉዳዮች ቢሮዎች ገልጸዋል፡፡ በተያያዘም በአዲስ አበባ በተካሄደው ታላቅ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የደረሰውን የቦንብ ፍንዳታ የድሬዳዋ አስተዳደር አውግዟል፡፡ አስተዳደሩ በመግለጫ በአደጋው ለተጎዱ ቤተሰቦች መጽናናትን የተመኘ ሲሆን አጥፊዎች ''በአስቸኳይ ለህግ መቅረብና ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለባቸው'' ብሏል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር በሰልፉ ላይ ድብቅ ዓላማ ያነገቡና የኢትዮጵያዊያንን ታላቅነትና ህብረት የማይፈልጉ አካላት ያደረሱት ጥፋት በእጅጉ የሚወገዝ መሆኑን ገልጿል፡፡ በሌላ በኩል የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ የምስጋናና የድጋፍ ሰልፉ ላይ በተፈጸመ የቦንብ ጥቃት ከፍተኛ ሀዘን እንደተሰማው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሰናይ አኩዎር ለኢዜአ ገልፀዋል፡፡ "ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለውን ድጋፍና ምስጋና ለመግለጽ በወጣው ህዝብ ላይ ችግር የፈጠሩት ሰዎች የአገሪቱን ሰላም፣ አንድነትና እድገት የማይፈልጉ ጸረ- ሰላም ኃይሎች ናቸው" ብለዋል። በመሆኑም የክልሉ ህዝብና መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሯቸው የሰላም፣ የአንድነትና የፍቅር እንቅስቃሴ ከዳር እንዲደርሱ የክልሉ መንግስትና ህዝብ ከጎናቸው መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም