ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሲ ኤን ኤን የ2019 ˝ጀግና˝ ፍሬወይኒ መብራህቱን አነጋገሩ

51
ኢዜአ፤ታህሳስ 14/2012 ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሲ ኤን ኤን የ2019 ˝ጀግና˝ ፍሬወይኒ መብራህቱን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ። ኢትዮጵያዊቷ ፍሬወይኒ መብራህቱ በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውሉ የሴቶች የፅዳት መጠበቂያዎችን ዲዛይን ያደረጉ እና የፈጠሩ ሴት ናቸው፡፡ በቅርቡም ታዋቂው የሚዲያ ተቋም የሲ ኤን ኤን የዓመቱ ˝ጀግና˝ ብሎ መርጧቸዋል። ይህን ተከትሎም ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋቸዋል። ወይዘሮ ፍሬወይኒ መብራሃቱ በዚህ ወቅት ሽልማቱ ስራቸውን ይበልጥ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ትልቅ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው ተናግረዋል። "ሽልማቱ እኔን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የኢትዮጵያ ሴቶች ያኮራ ነው" ብለዋል። በቀጣይም ስራቸውን ለበርካታ ሴቶች ተደራሽ ለማድረግ የበኩላቸውን እንደሚጥሩም ገልጸዋል። ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ይህ ውጥናቸው እንዲሳካ የበኩላቸውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን እንደገለጹላቸውም ጨምረው ተናግረዋል። ፍሬወይኒ መብርሃቱ ሽልማቱን እንዲያገኙ ድምጽ በመስጠት ጭምር ድጋፍ ላደረጉ ኢትዮጵያውያን ፕሬዝዳንቷ ምስጋና አቅርበዋል። ፍሬወይኒ በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውሉ የሴቶች የፅዳት መጠበቂያዎችን ለማምረት በከፈቱት ፋብሪካ ከ50 በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የሥራ እድል የፈጠሩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ከ90 በመቶ በላይ ሴቶች ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም