መገናኛ ብዙሃን ከግጭት ጋር በተያያዘ የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች ግጭቱን ከማርገብ ይልቅ የሚያባብሱ ናቸው - ጥናት

77
ኢዜአ ታህሳስ 14/2012 በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ግጭቶችን የሚዘግቡበት መንገድ ችግሩን ከማርገብ ይልቅ ለአንዱ ወገን በማድላት ግጭቱ እንዲባባስ የሚያደርጉ ናቸው ሲል አንድ ጥናት አመለከተ። ጋዜጠኞች ከፍርሃት ቆፈን ወጥተው ሃሳባቸውን በነጻነት መግለጽ ቢችሉም መገናኛ ብዙሃን ውስጣዊ ብዝሃነትን በበቂ ደረጃ ማስተናገድ አልቻሉም ይላል ጥናቱ። ይህን ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የመንግስትና የግል የህትመትና ብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ዙሪያ ያላቸውን ሚና በተመለከተ 'ደበበ ሃይለገብርኤል የህግ ጽህፈት ቤት"  የተሰኘ የግል ኩባንያ ያካሄደው ጥናት ነው። ጥናቱ በአዲስ አበባ ተከስቶ የነበረውን ግጭት፣ በከፍተኛ ባለስልጣናትና የጦር መኮንኖች ግድያ፣ በጉጂ ዞን ተፈናቃዮችና በክልሎች መካከል የተፈጠረውን የቃላት ጦርነት በተመለከተ የተሰሩ ዘገባዎችን ዳሷል። ከዚህም ሌላ ጥናቱ 88 የድምጽና ምስል ዘገባዎችን፣ የግል የህትመት ውጤቶችንና በዘርፉ የካበተ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን አስተያየት በናሙናነት በመውሰድ ለመተንተን ሞክሯል። የጥናቱ አቅራቢና በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር አቶ ፍሬዘር እጅጉ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ የመገናኛ ብዙሃን ወደሥራ መግባት በመጀመራቸው የሚዲያ ውጫዊ ብዝሃነት አድጓል። ጥቂት መገናኛ ብዙሃን የግጭት ዘገባዎችን በሚያጠናቅሩበት ወቅት ሰላማዊና መፍትሄ ጠቋሚ መንገድን የሚከተሉ መሆናቸው በመልካም ጎኑ ይነሳል ብለዋል። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ የህዝብን ጥቅም ከማስጠበቅ ይልቅ የራሳቸውን ፍላጎት ለማርካት ሲገለገሉበት ይታያል ሲሉ አመልክተዋል። የህግ ባለሙያው አቶ ደበበ ሀይለገብርኤል አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ሙያውን መተግበር ተስኗቸው የጥቂት ቡድኖች አንደበት በመሆን እያገለገሉ ነው ይላሉ። ከዚህም ሌላ ሚዲያዎቹ የተለያየ አመለካከት ያላቸው አካላትን አቅርቦ በሃሳብ እንዲሟገቱ ከማድረግ ይልቅ ውስጣዊ ብዝሃነትን ማስተናገድ ተቸግረው የራሳቸውን አቋም ሲያራምዱ ነው የሚስተዋለውም ብለዋል። የጥናቱ አቅራቢ አቶ ፍሬዘር እጅጉ በኢትዮጵያ ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የመገናኛ ብዙሃን ሚና የጎላ በመሆኑ ተቋማቱ ብዝሃነትን በማስተናገድ ልዩነቶች እንዲጠቡ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። አቶ ፍሬዘር "የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃንን ለፓርቲ ስራ ብቻ የተቋቋሙ፣ በስውር ፓርቲዎች የሚመሩና ሃይማኖትን፣ ብሄርን ወይም ሌላ ቡድንን መሰረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ" ብለው ይከፍሏቸዋል። በመሆኑም ተቋማቱ ከዚህ በመውጣት ነጻ፣ ገለልተኛና በህዝብ ዘንድ ተዓማኒ ሆነው እንዲቀጥሉ የተቋማት አደረጃጀትና ፖሊሲዎችን መፈተሽ አለባቸው ብለዋል። መገናኛ ብዙሃን ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዲችሉ ነፃና ገለልተኛ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል። የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በበኩላቸው በመገናኛ ብዙሃን የሚታየውን ችግር መፍታት የሁሉንም ቁርጠኝነት ይጠይቃል ብለዋል። "ከዜጠኞችና የመገናኛ ብዙሃን ተቋማቱ የራሳቸውን ስራ ይስሩ፤ ተደራጅተው ይሞግቱ፤ መንግስት ይሄን ለመደገፍ ዝግጁ ነው" ብለዋል ዶክተር ጌታቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም