መንግስት የወጪ ንግድ ችግሮችን እያወቀ መፍታት ያለመቻሉ እንዳሳሰባቸው የዘርፉ ተዋናዮች ገለጹ

50
ኢዜአ ታህሳስ 14/2012 መንግስት ባለፉት ዓመታት በተከታታይ እያሽቆለቆለ የመጣውን የወጪ ንግድ ችግር እያወቀ መፍትሔ መስጠት ያለመቻሉ እንዳሰሰባቸው ላኪዎች ተናገሩ። በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አዘጋጅነት የማንፋክቸሪንግ ምርት የ10 ዓመት የወጪ ንግድ አፈጻፀምን የሚዳስስ ውይይት ተካሄደ። የውይይቱ ተሳታፊ የዘርፉ ተዋናዮች እንደገለጹት፤ መንግስት ላለፉት አስራ ሁለት ዓመታት እያሽቆለቆለ   የመጣውን የወጪ ንግድ ችግር እያወቀ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አልቻለም። ባለሃብቶቹ እንደጠቆሙት፤ እነዚህ ችግሮች ሲንከባለሉ ከመቆየታቸው ባሻገር አዳዲስ ችግሮችም ተጨምረዋል። የውጪ ምንዛሬ እጥረት፣ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ የወደብ ኪራይ ማሻቀብ እንዲሁም የሎጂስቲክስና የጉምሩክ አገልግሎት መወሳሰብ ዋነኛ ችግሮች መሆናቸውን ተወያዮቹ አንስተዋል። በተጨማሪም የሰራተኛ ፍልሰትና የሰለጠነ ሰራተኛ እጦት፣ የጥጥ ምርት እጥረት፣ የመለዋወጫ ችግር፣ ህገ ወጥ እንቅስቃሴና አጠቃላይ የግብዓትና የምርት እጥረት የተለዩ ችግሮች እንደሆኑ ገልጸዋል። ከባንክ ወለድ ጋር በተያየዘም ልማት ባንክ የጣለው 12 በመቶ ወለድ እየከበዳቸውና ምርቶችን በኪሳራ እየላኩ እንደሆነም ያስረዳሉ። ባለሃብቶቹ 'የቮውቸር' (ልዩ ተጠቃሚ የሚያደርግ ደረሰኝ) ስርዓት ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ ወጥነትና የተናበበ የአሰራር ስርዓት አለመኖር የወጪ ንግዱን እንዳይንቀሳቀስ እንዳደረጉት ነው የተናገሩት። መንግስት ከሞላ ጎደል ችግሩን እያወቀ ለማቃለል እያደረገ ያለው ጥረት ማነስና በአጠቃላይ የምርት እጥረት ባለበት ሁኔታ የወጪ ንግዱን ማሳደግ ከባድ መሆኑንም አንስተዋል። በሌላ በኩል አንዳንድ ምርቶች በውጪ ገበያ ካላቸው ዋጋ ይልቅ የአገር ውስጥ ዋጋቸው ከፍተኛ መሆን ኤክስፖርቱን እያደከመው ነው ተብሏል። ለአብነትም የአንድ ኪሎ ስጋ ዋጋ በዓለም ገበያ 3 እስከ 4 ዶላር ሲሆን፤ የአገር ውስጥ ገበያው ግን ወደ 10 ዶላር ገደማ መሆኑም አንስተዋል። ችግሩ በባህሪው ውስብስብና አሳሳቢ በመሆኑ መንግስት ሁሉንም ባለድርሻዎች ያሳተፈ ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑን የንግድና አንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረየሱስ ይናገራሉ። እስካሁንም መንግስት የዘርፉ ተዋናዮች ተቀራርበው በመስራት ችግሩን እንዲያቃልሉ ለማድረግ ሲሰራ እንደቆየም አመልክተዋል። ''እየተካሄደ ያለው ውይይትም ለሰነዱ ግብዓት ይሆናል'' ያሉት አቶ ተካ፤ ''አሁን በጣም ወሳኝ ጊዜ ላይ በመሆናችን ዘርፉን በአግባቡ መምራት የሚያስችል ሰነድ ተዘጋጅቷል'' ብለዋል። ሰነዱ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ የገለጹት አቶ ተካ፤ የወጪ ንግዱን አቅጣጫ ለመምራትና ችግሩንም ለማቃለል እንደሚያስችል አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም