ትእምት በበጎ ተግባራት ለተሰማሩ ድርጅቶችና ማህበራት 205 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

75
ኢዜአ ታህሳስ 14/2012 የትግራይ መልሶ ማቋቋም ድርጅት /ትእምት/ በበጎ ተግባራት ለተሰማሩ ከአስር በላይ ድርጅቶችና ማህበራት ዛሬ 205 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ። ድርጅቱ ድጋፉን ያደረገው በትግራይ ክልል በተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት ተሰማርተው የላቀ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ለሚገኙ ነው። በድርጅቱ የምግባረ ሰናይ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ታረቀ እንዳሉት ድጋፉን ያደረጉት በኤችአይቪ/ኤድስ መከላከል፣ አረጋውያን፤ ህፃናትናየ አእምሮ ህሙማንና አካልጉዳተኞችን በመደገፍ በጎ ስራ የተሰማሩ ድርጅቶች እና ማህበራት የጀመሩትን ስራ እንዲያጠናክሩ ለማበረታታት ነው። ድርጅቶቹና ማህበራቱ የህብረተሰብን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለል የሚያደርጉት ጥረት የገንዘብ ድጋፉ እገዛ እንደሚኖረው ተናግረዋል። የአባ ፍረ ሚናጦስ የህፃናትና አረጋውያን እንክብካቤ ማዕከል ስራ አስኪያጅ አባ ገብረመድህን በርሀ በበኩላቸው የተደረገላቸው የአራት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማዕከሉ ያለበትን የመኝታ ክፍሎች ችግር ለማቃላል እንደሚረዳው ተናግረዋል። "የወተት ላሞችን በመግዛት በማዕከሉ ውስጥ የሚረዱ ህጻናትና አረጋዊያንን የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት እንዲሟላላቸውም የገንዘብ ድጋፉ እጅግ አስፈላጊ ነው "ብለዋል። "ያገኘነው የ500ሺህ ብር ድጋፍ የማህበራችን አባላት የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ሞራላቸውን ተጠብቆ ከህብረተሰቡ ጋራ ሳይሸማቀቁ አብረው እንዲኖሩ ያግዛቸዋል" ያሉት ደግሞ በደማቸው ውስጥ የኤች አይ ቪ/ኤዲስ ቫይረስ ያለባቸው ማህበራት ሊቀመንበር አቶ ብርሃነ በረሁ ናቸው። የቫይረሱ ተጠቂዎች ገቢ የሚያገኙበት ስራ ከማመቻቸት ባለፈ ህብረተሰቡ ከበሽታው እንዲጠበቅ ለማስተማር የገንዘብ ድጋፉ እንደሚያግዛቸውም ገልጸዋል። የታጋዮች ማህበር ስራ አስከያጅ  ነባር ታጋይ  ይፈናን አብርሃ በበኩላቸው ያገኙት 10 ሚሊዮን ብር በትጥቅ ትግሉ ወቅት የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍ እንደሚጠቅማቸው ተናግረዋል። የትግራይ መልሶ ማቋቋም ተቋም /ትእምት/  ባለፉት አምስት ዓመታት የህብረተሰቡ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለማቃለል ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም