በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች እውቅናና ሽልማት ተሰጠ

74
ኢዜአ ታህሳስ 14/2012.. የዘንድሮው አዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት፣ በጨዋታው የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች እውቅናና ሽልማት ተሰጠ። በአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ዋንጫ ሰለሃዲን ሰኢድ ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ ተሸልሟል። የዘንድሮው 14ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 14 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ስምንት ክለቦችን በማሳተፉ መካሄዱ ይታወሳል። የጨዋታው ኮከብ ተጫዎቾችና አሰልጣኞችም ተሸልመዋል። ሽልማቱን የሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ነው። በዚህም መሰረት በውድድሩ አራት ጎል በማስቆጠርና በጨዋታውም ምርጥ ጎል በማግባት የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሰለሃዲን ሰኢድ ተሸላሚ ሆኗል። የጨዋታው ኮከብ ተጫዋች ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናው ፈቱዲን ጀማል ሆኗል። እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቪጅሆቭ ኮከብ ተብሎ ተሸልሟል። በጨዋታው ለተሳተፉ ክለቦችም እንደየደረጃቸው ከ150 ሺህ እስከ 750 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በዚህ የምስጋና እና እውቅና ዝግጅት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሀገሪቱ እግር ኳስ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ ነው ላላቸው ግለሰቦችና ተቋማትም ልዩ የዋንጫ ሽልማት አበርክቷል። በዚህ ልዩ ሽልማት እውቅና ከተሰጣቸው ግለሰቦች መካከል ከ30 ዓመት በላይ በእግር ኳስ ሜዳዎች በመገኘት   እግር ኳስን በመመልከትና በሬዲዮና ህትመት ጋዜጠኝነት ሙያ እያገለገለ የሚገኘው ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ይገኝበታል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾችና አሰልጣኝ የነበሩት አስራት ሃይሌ፣ የቀድሞ የእግር ኳስ ዳኛ አሁን ላይ ደግሞ በኮሚሸነርነት እያገለገሉ ያሉት ጌታቸው ሃይለማሪያም፣ የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱና ጋዜጠኛ ሰኢድ ኪያር ከልዩ ተሸላሚዎች መካከል ናቸው። ከተቋማት ደግሞ ዳሽን ቢራ በአሞሌ አማካኝነት ተመልካቾች ሳይጉላሉ በየቤታቸው ሆነው ትኬት ቆርጠው እንዲገቡ በማድረግ ላበረከተው አስታዋጽኦ ተሸላሚ ሆኗል። ውድድሩን በቀጥታ ሲያስተላለፍ የነበረው አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በተመሳሳይ ልዩ ተሸላሚ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም