ከድህነትና ኋላቀርነት የተላቀቀች ኢትዮጵያን ለመገንባት የድርሻችንን እንወጣለን - ወጣቶችና ምሁራን

85
መቀሌ ሰኔ 16/2010 ከድህነትና ኋላቀርነት የተላቀቀች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ ግንባር ቀደም ተዋናይ እንደሚሆኑ በትግራይ ክልል የሚገኙ ወጣቶችና ምሁራን አረጋገጡ። ምሁራንና ወጣቶች ይህንን ያረጋገጡት ትናንት የትግራይ ሰማእታት ቀንን ምክንያት በማድረግ በመቀሌ ሰማእታት ሐውልት በተካሄደው የፓናል ውይይት ማጠቃላያ ላይ ነው። ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና በክልሉ ከሚገኙ ወረዳዎች የተውጣጡ ወጣቶችና ምሁራን እንዳሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ብልፅግና ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና አላቸው። ለተግባራዊነቱም ኢትዮጵያን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ በተጀመረው ርብርብ ላይ ድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል፡፡ በፓናል ውይይቱ ላይ ከተገኙ ተሳታፊዎች መካከል የወላይታ ተወላጅና በአክሱም ዩኒቨርስቲ የጂኦግራፊ መምህር ዶክተር ክበም ዴታም በሰጡት አስተያየት ትናንት  ወጣቶች በከፈሉት መስዋትነት ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ  የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት ተረጋግጧል፡፡ “የህዝቦች የአንድነታቸው ሚስጥርም ለህዝባቸው ክብርና ጥቅም በማስቀደምና በዓላማ ጽናት ትናንት ወጣቶች የከፈሉት የህይወት መስእዋትነት ነው'' ብለዋል። ‘‘እኛም የህዝባችን ጥቅም ሲረጋገጥ የግላችን ጥቅም ይረጋገጣል የሚል ጽኑ እምነት ይዘን በመስራትና በትምህርትና በቴክኖሎጂ የበለፀገ አገር ተረካቢ ዜጋ ለማፍራት የበኩላችንን ሚና እንጫወታለን'' ብለዋል ዶክተር ክበም። የትግራይ ወጣቶች ማህበር አባል ወጣት አማኑኤል ወልደማርያም በበኩሉ፣ “ለዜጎቿ ምቹ የሆነች አገር መገንባት የምንችለው ለመብታችን መከበር እየታገልን የተጣለብን ግዴታ መወጣት ስንችል  ነው'' ብሏል። ወጣት አማኑኤል እንዳለው፣‘‘አብረን ለመልማት አብረን መስራት ይጠበቅብናል‘‘ በማለት አስተያየቱን ገልጿል። ሌላዋ የመቀሌ ከተማ ወጣት ራሄል ደስታ እንዳለችው አገሪቱ ድህንትን ለማጥፋት በምታደረግው ርብርብ ድርሿዋን እንደምትወጣ አረጋግጣለች። “እኛም የሰራነውን መልካም ነገር ይበልጥ ማጠናከር ይጠብቅብናል'' ያለችው ወጣቷዋ በሁሉም ዘርፍ በተደረጃ መልክ በመታገል የማይፈታ ችግር እንደሌለ ተናግራለች። የ1960ዎቹን ወጣቱ ትውልድ እና ጀግንነትን አስመልክተው የፓናል የመነሻ ፅሁፍ ያቀረቡ የህወሓትት/ ኢህአደግ መስራች ነባር ታጋይ አባይ ፀሃዬ በበኩላቸው ''ለህዝብ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ መረጋገጥ ሲሉ የትናንት ወጣቶች የህይወት መስዋእትነት ባይከፍሉ የአሁኑ ውጤት ማየት ፍጹም ባልታሰበ ነበር'' ብለዋል። “ስለዚህ የመጨረሻ የትናንት ወጣቶች ግብ ፀረ ሰላም የነበረውን የደርግ ስርዓት መገርሰስ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጰያ ውስጥ ድህነትና ኋላ ቀርነት ተወግዶ ማየት ነው'' ብለዋል። ‘‘የዘመኑ ትውልድና ተጠቃሚነት፣ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ መንገዶች’’ የሚል ፅሁፍ ያቀረቡት የትግራይ ክልል ግብርናና  ገጠር ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አትንኩት መዝገቡ በበኩላቸው “ነባሩ ትውልድ ራሱ መስዋእት በመሆን በተቀደጀናቸው ድሎች የዛሬው ትውልድ  ከጠባቂነት ለማላቀቅ እያስቻለ ነው'' ብለዋል። በመሆኑም በመቶ ሺህ የሚገመት የገጠርና የከተማ ወጣቶች በተፈጠረላቸው የብድርና የገበያ ትስስር በመጠቀም ወደ ባለሃብት እየተሸጋገሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የማያቋርጥ ትግል የሚያስፈልገው የመልካም አስተዳደርና የተቀላጠፈ የልማት አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች መኖራቸውን ዶክተር አትንኩት አመልክተዋል። ችግሮቹን ለመፍታትም በአዲስ መልክ ትግል መጀመሩን ነው ያስታወቁት ዶክተር አትንኩት። የፌዴራሊዝም ስርዓት ያስገኘው ጥቅም አስመልክተው ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ በበኩላቸው “ስርዓቱ በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያን ለመገንባት አስችሏዋል'' ብለዋል። እንዲሁም በህዝቦች መካከል እኩልነት እንዲረጋገጥና ህዝቦች በሙሉ ፈቃደኝነታቸውና ፍላጎታቸው ላይ ጠንካራ አንድነት እውን እንዲሆን መንገድ ከፍቷል ነው ያሉት አቶ አስመላሽ። በተካሄደው የፓናል ውይይት አንድ ሺህ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም