የጎባ ከተማ ነዋሪዎች በሞጣ የእምነት ተቋማት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አወገዙ

111

ኢዜአ ታህሳስ 14/2012  በባሌ ዞን የጎባ ከተማ ነዋሪዎች በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ በቅርቡ በእምነት ተቋማት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አወገዙ።

ነዋሪዎቹ ድርጊቱን ያወገዙት ዛሬ ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ነው።

ሰልፈኞቹ በቤተ እምነቶች ላይ የሚደረግ ጥቃት ማንኛውንም ኃይማኖት የማይወክልና የሚኮንን ተግባር እንደሆኑ ባሰሙት መፈክርና በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ሀሰን አብደላ “ኢትዮጵያ ሁሉም እምነቶች አብረው በእኩል የሚኖሩባት ሀገር መሆኗ መታወቅ አለበት “ብሏል።

በእምነት ተቋማት ላይ ጥቃቶችን የሚፈጽሙት የእምነት እኩልነትን መቀበል የሚከብዳቸው ጽንፈኞች መሆናቸውን ተናግሯል።

በቅርቡ በሞጣ ከተማ የተፈጸመው ድርጊት የትኛውንም እምነት እንደማይወክል የገለጹት ደግሞ ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ አቶ ታደሳ ከተማ ናቸው፡፡

ይህም የሀገሪቱን ሰላምና አንድነት በማይፈለጉ አካላት የተፈጸመ እኩይ ድርጊት መሆኑን በመጥቀስ ድርጊቱን አውግዘዋል።

“ ህዝቡ በከፋፋዮች አጀንዳ ሳይታለል ከምንጊዜውም በላይ አንድነቱን ማጠናከር አለበት” ብለዋል፡፡

መንግስት በሞጣ ከተማ ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተ ዕምነቶች ህብረተሰቡን በማስተባበር መልሰው እንዲሰሩ በማድረግ ለአብሮነት ያለውን ጠንካራ አቋም እንዲያሳይም ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል።

የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሀጂ በበኩላቸው ህዝቡ የጥፋት ኃይሎች በሚፈጥሩት አጀንዳ ሳይታለል አንድነቱንና አብሮነቱን ከመቼውም ጊዜ በላይ በማጠናከር ለሀገሪቱ ሰላምና ብልጽግና የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

አስተዳዳሪው እንዳሉት ሀገርን ማልማትም የሚቻለው ሁሉም ተከባብሮና ተደጋግፎ መኖር ሲችል በመሆኑ የጥፋት ኃይሎችን ሴራ ለማክሸፍ ሁሉም የበኩሉን መወጣት ይኖርበታል።

በሰላማዊ ሰልፉ ከጎባ ከተማና አካባቢዋ የተውጣጡ የእስልምናና የክርስትና እምነት ተከታዮች መሳተፋቸውን ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም