በግድቡ ዙሪያ በካርቱም የተካሄደው ውይይት ስኬታማ ነበር - ዶክተር ስለሺ በቀለ

45

ኢዜአ ታህሳስ 14 ቀን 2012 በኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ሰሞኑን በሱዳን ካርቱም የተካሄደው የሶስትዮሽ ውይይት ውጤታማ እንደነበር የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ገለፁ።

ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ በቀለ የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የውሃ ሚኒስትሮች በካርቱም ያካሄዱት ውይይት ውጤታማ እንደነበር ዛሬ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድና የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታ አልሲሲ በሩሲያ ሶቺ ከተማ ተገናኝተው ግድቡን በተመለከተ አራት ድርድሮችን ለማካሄድ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።

በስምምነቱ መሰረትም በአዲስ አበባ የመጀመሪያው ድርድር የተካሄደ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሱዳን ካርቱም ከታህሳስ 11 ቀን 2012 ዓም ጀምሮ ለሁለት ቀናት ተካሂዷል።

ድርድሩ በመሰረታዊነት ያተኮረባቸው ጉዳዮች የግድቡ የውሃ አሞላል ሂደት፣ የውኃ አለቃቀቅ፣ ከሙሌት በኋላ ያለው የግድቡ ኃይል የማምረት ተግባርና ድርቅ ቢከሰት የወንዙን ውሃ እንዴት ማስተዳደር ይቻላል የሚሉት ናቸው።

በእነዚህ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የተካሄደው ድርድር በርካታ ውጤቶች የተገኙበት መሆኑን ነው ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ የገለፁት።

ከዚህ በፊት የግድቡ ውሃ አሞላልንና ዓመታዊ ፍሰትን ጨምሮ በግብጽ በኩል የቀረቡት የመደራደሪያ ሀሳቦች እንዲነሱ መደረጉን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

ግብጽ አቅርባው በነበረው ሀሳብ አማካይ ዓመታዊ የውሃ ፍሰት 49 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሚትር እንዲሆን፤ እንዲሁም የአሱዋን ግድብ ከፍታ 165 ሜትር እንዲጠበቅ የሚሉት ይገኙበታል።

ግብጽ ተፈጥሮአዊ ፍሰት የሚል አዲስ መደራደሪያ ሀሳብም አቅርባ እንደነበር ሚኒስትሩ አስታውሰው ይህም በኢትዮጵያ በኩል ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ እንዲቀር ሆኗል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የአለም ባንክና የአሜሪካ መንግስት ተወካዮች በታዛቢነት ተገኝተዋል።

የሶስቱ አገራት ባለስልጣናት በግድቡ የቴክኒክ አፈፃፀምና አተገባበር ላይ ሲመክሩ ይህ ለስምንተኛ ጊዜ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም