የዓይደር ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ማዕከል ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ነው

74

ኢዜአ ታህሳስ 14 ቀን 2012 በዓይደር ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ በመገንባት ላይ ያለው የካንሰር ሕክምና ማዕከል ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተገለጸ።

ማዕከሉ ከስድስት ወራት በኋላ ለህብረተሰቡ የካንሰር ሕክምና አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም ተመልክቷል።

በሆስፒታሉ የማዕከሉ አስተባባሪ ዶክተር ክብሮም ሕሉፍ ለኢዜአ እንዳሉት፣ ለማዕከሉ እየተገነቡ ካሉት ዘመናዊ ሕንጻዎች መካከል አብዛኞቹ ተጠናቀዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመት መጨረሻ ወር ላይ ዘመኑ የደረሰበትን የጨረር ሕክምና ጨምሮ ከካንሰር ጋር የተያያዙ የመቅኒ ምርመራ፣ የቀዶ ሕክምናና ሌሎች የጤና አገልግሎቶችን ማዕከሉ መስጠት እንደሚጀምርም ገልጸዋል።

ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በትግራይ ክልል የካንሰር ህሙማን ለህክምና ወደአዲስ አበባ ያደርጉት የነበረውን ጉዞ ሙሉ በሙሉ እንደሚያስቀርላቸው ተናግረዋል።

ለማዕከሉ የሚሆን የጨረር ህክምና መስጫ ማሽን በአሁኑ ወቅት ሆስፒታሉ ውስጥ መድረሱን የገለጹት ዶክተር ክብሮም፣ በቀጣይ ተከላውን በውጭ ባለሙያዎች ታግዞ ለማከናወን አስፈላጊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ በትግራይ ክልል ከሚከሰቱ የካንሰር በሽታዎች መካከል የጡት፣ የማህፀን፣ የአንጀት እና የደም ካንሰር የሚጠቀሱ ናቸው።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የካንሰር ህሙማን በበኩላቸው የካንሰር ሕክምና ማዕከሉ ግንባታ ሥራ መጠናቀቅ ለበሽታው ተጠቂዎች ብሩህ ተስፋ መፈንጠቁን ተናግረዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ምስግና ኃይሉ፣ ያለባቸውን የአንጀት ካንሰር በሽታ ለመታከም በአዲስ አበባ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በየጊዜው እንደሚመላለሱ ተናግረዋል።

ይህም ከፍተኛ ወጪ ከማስወጣት ባለፈ በወረፋ ብዛት መጉላላት እንዲደርስባቸው ማድረጉን ገልጸዋል።

"በአሁኑ ወቅት በአቅራቢያችን ሕክምና የምናገኝበት ማዕከል መቋቋሙ ተስፋችንን ብሩህ አድርጎታል" ብለዋል።

"ለሕክምና ወደአዲስ አበባ ለመመላለስ የምናወጣውን ከፍተኛ ወጪ በማስቀረት በአቅራቢያችን ሕክምናው የምናገኝበት ዕድል በመፈጠሩ ተደስቺያለሁ" ያሉት ደግሞ የጡት ካንሰር ታማሚዋ ወይዘሮ ፅጌረዳ ገብረአምላክ ናቸው።

በስኳር በሽታ የታመሙት ዲያቆን እስጢፋኖስ ሐረጎት በበኩላቸው፣ "ማዕከሉ ለካንሰር በሽታ ተጠቂዎች ብቻ ሳይሆን ለስኳር ሕሙማንም ጭምር ትልቅ ተሰፋ ነው" ብለዋል።

የካንሰር ማዕከሉ በጡት፣ በማህፀንና በሌሎች የካንሰር በሽታዎች የሚሰቃዩ ሰዎችን በመድኃኒትና በጨረር ሕክምና ለማዳን አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑንና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ትልቅ ድርሻ እንዳለው የገለጹት ደግሞ በዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ጠቅላላ ኃኪም የሆኑት ዶክተር ዮሴፍ አዳነ ናቸው።

ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የትግራይ ክልልን ጨምሮ ለአማራ ክልል አጎራባች ወረዳዎችና ለአፋር ክልል ታማሚዎች አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የካንሰር ህክምና ማዕከሉ ግንባታ ከአራት ዓመታት በፊት መጀመሩ ለማወቅ ተችሏል።

የዓይደር ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ስር የሚገኝና የትግራይ ክልል ብቻኛ ሪፈራል ሆስፒታል መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም