በህገ ወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ የውጭ ንግድ ገቢ እየቀነሰ ነው

105
ኢዜአ ታህሳስ 14 / 2012... በህገ ወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት ወደ ወጭ ከሚላኩ ምርቶች የሚገኘው ገቢ እየቀነሰ መምጣቱን በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን የመቀሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስከያጅ አቶ ምህረትአብ ገብረመድህን ለኢዜአ እንደገለጹት የህገ ወጥ ንግድ መስፋፋት ከክልሉ ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ ሰሊጥ፣ እጣንና ሌሎች የግብርና ምርቶችና የቁም እንስሳት እየተገኘ ያለውን ገቢ እየቀነሰ እንዲመጣ አድርጎታል ። ከዘርፉ እየተገኘ ያለው ገቢ በተለይም ካለፉት ሰባት አመታት ወዲህ እየቀነሰ መሆኑን ተናግረዋል። በ2006 ዓም ስድስት ወራትና ከክልሉ ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶችና ቁም እንሰሳት ሽያጭ 63 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተገኝቶ እንደነበር አስታውሰዋል። በዚህ አመት አምስት ወራት ከዘርፉ 35 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ለአብነት ጠቅሰዋል ። በተመሳሳይ ከሰባት አመታት በፊት ከክልሉ እስከ 18 ኩንታል ወርቅ ለሔራዊ ባንክ ይቀርብ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ እየቀረበ ያለው አንድ ኩንታል የማይሞላ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል ። ከክልሉ የግብርና ምርቶችን ጨምሮ ወርቅ ወደ ተለያዩ ውጭ ሀገራት በኮንትሮባንድ እንደሚወጣ ጠቁመዋል። ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ የሀገርን ገቢ ከመጉዳት ባለፈ የሰላምና ጸጥታ ስጋት እየሆኑ ነው" ያሉት ስራ አስኪያጁ በክልሉና በባለስልጣኑ መካከል የተቀናጀ አሰራር አለመኖሩ ለችግሩ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል። ችግሩን ለመፍታት ባለስልጣኑ ከክልሉ የጸጥታና የሚዲያ አካላት እንዲሁም በየደረጃው ከሚገኙ የአስተዳደር መዋቅሮች ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስርዓት ወደ ተግባር መገባቱን ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል ። የክልሉ ገቢዎች ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አሰፉ ሊላይ ኮንትሮባንድ ንግድ ብቻ ሳይሆን ደረሰኝ አለመቁረጥ፣ ግብር መሰወርና ሌሎች በክልሉ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች መሆናቸውን ተናግረዋል። "ከክልሉ የሚሰበሰብ ግብር የክልሉን 60 በመቶ በጀት መሸፈን ሲገባው ከ35 በመቶ ማለፍ አልቻለም" ብለዋል። ችግሩን ለመፍታት መብቱን የሚጠይቅ ብቻ ሳይሆን ግዴታውን ጭምር የሚወጣ ማህበረሰብ ለመፍጠር በጋራ መስራት ማስፈለጉን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም