በጎፋ ዞን በኮሌራ አራት ሰዎች ሞቱ

53

ሶዶ ታኅሣሥ 14 /2012 በጎፋ ዞን የተከሰተው የኮሌራ በሽታ አራት ሰዎች መሞታቸውን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ።

በሽታውን ለመቆጣጠር ልዩ ግብረ ኃይል መቋቋሙን ገልጿል።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት ሰዎቹ የሞቱት በዑባ ደብረ- ጸሐይና ዛላ ሁለት ወረዳዎች ነው።

ለሰዎቹ በተደረገው የላቦራቶሪ ምርመራ በበሽታው ሕይወታቸው ማለፉን ተረጋግጧል ብለዋል።

በበሽታው የተጠቁ 119 ነዋሪዎች በተቋቋሙ ሁለት ጊዜያዊ የክትትልና ድጋፍ  ማዕከላት ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን አቶ ዓለማየሁ አስረድተዋል።

በሽታው የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ልዩ ግብረ ኃይል መቋቋሙን ገልጸዋል።

በሽታው የተከሰተባቸው አካባቢዎች ነዋሪዎች ውሃ አፍልቶ አንዲቀጠሙና የአካባቢና የግል ንጽሕና እንዲጠብቁ ኃላፊው አሳስበዋል።

መምሪያው በሽታውን ለመከላከል በሚያደርገው እንቅስቃሴ የሕክምና ቁሳቁስና ግብዓቶች ድጋፍ እንዲደረግለት ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም