ዶክተር አብይ አህመድ ለአገራዊ መግባባት፣ ለፍቅርና ለይቅርታ የሰጡት ትልቅ ቦታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፍ እናደርጋለን...የጎንደር ነዋሪዎች

57
ጎንደር ሰኔ 16/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለአገራዊ መግባባት፣ ለፍቅርና ለይቅርታ የሰጡት ትልቅ ቦታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፋችን አይለያቸውም ሲሉ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ዛሬ ባከሄዱት የድጋፍ ሰልፍ አስታወቁ፡፡ ቁጥራቸው በብዙ ሺህ የሚገመት የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በከተማው ዋና ዋና መንገዶች በመዘዋወር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ድጋፍ በሰላማዊ መንገድ ተጠናቋል። በሰልፉ ላይ ከተገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ወጣት ቢኒያም ሰለሞን በሰጠው አስተያየት " ወጣቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ እርምጃ በመደገፍ ከጎናቸው ይቆማል " ብሏል፡፡ "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ አንድነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያሳዩት ጽኑ አቋም አስደስቶኛል፤ ዛሬ በሰልፉ የተቀላቀልኩትም ይህን በመደገፍ ነው" ያሉት ደግሞ አቶ አለባቸው መኩሪያ የተባሉ የከተማው ነዋሪ ናቸው፡፡ "አገራችን በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን ያቀፈች እንደመሆኗ በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተውን የቀደምት ታሪካዊ እሴቶች ማጠናከር ከምንም በላይ የወቅቱ አጀንዳ ነው" ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ  ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያከናወኗቸው ተግባራት የህዝቡን የለውጥ እንቅስቃሴ እንዳቀጣጠለው የገለጹት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ መሳፍንት ካሴ ናቸው፡፡ ህዝቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጀመሩት የለውጥ ጅማሮ አጋርነቱን በተግባር እንደሚያረጋግጥ የገለጹት አቶ መሳፍንት "የለውጥ እርምጃው እንዳይቀለበስ  እኔም ሆንኩ መላ ህዝቡ የለውጥ ኃይሉን በመደገፍ እንረባረባለን" ሲሉ ተናግረዋል፡፡ "ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገራችን ለረጅም ዓመታት ደብዝዞ የነበረውን ኢትዮጵያዊነት ፍቅርና አንድነት ዳግም እንዲጠናከር የጀመሩት ጥረት አስደስቶኛል" ያለችው ደግሞ ወጣት ሳምራዊት ቤተልሄም ናት፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁርጠኝነት የተጀመረውን የዴሞክራሲ የለውጥ ጉዞ ከግቡ ስለማያደርስ ህዝቡ ከዳር አስከዳር የጀመረውን ህዝባዊ ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ወጣት ሳምራዊት ገልጻለች፡፡ በህዝባዊ የድጋፉ ሰልፉ ላይ " ስር ነቀል ለውጥ ጊዜ የሚሰጠው አይደለም"፣ " ጊዜው የፍቅር ነው" ፣" ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ሁላችንም በጋራ እንቆማለን’’ የሚሉና የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ ጅማሮ የሚደግፉ በርካታ መፈክሮች ተስተጋብተዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶችም ሰላምና አንድነትን የሚሰብኩ መልእክቶችን አስተላልፈዋል፡፡ ሰልፈኞቹ በአዲስ አበባ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመደገፍና ለሰሯቸው ስራዎች ምስጋና ለማቅረብ ሰልፍ በወጡ ንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን የቦንብ ጥቃትም በጽኑ አውግዘዋል፡፡ በከተማው የተካሄደው የድጋፍ ሰልፉም ያለአንዳች የጸጥታ ችግር በሰላም ተጠናቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም