ኢትዮጵያ በመጪዎቹ 15 ዓመታት አስር ሳተላይቶችን የማምጠቅ እቅድ እንዳላት አስታወቀች

71

ኢዜአ ታህሳስ 14/2012.. ኢትዮጵያ በመጪዎቹ 15 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ አስር ያህል ሳተላይቶችን ወደህዋ የማምጠቅ እቅድ እንዳላት የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ሳተላይት 'ETRSS-1' ባለፈው ዓርብ ማለዳ ወደህዋ መምጠቋ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ የኢንስቲትዩቱ  ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይን ጨምሮ የተቋሙ አመራሮች የሳተላይቷን አሁናዊ ሁኔታ የተመለከተና ቀጣይ ስራዎችን የሚዳስስ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ በስፔስ ዘርፍ ተገቢውን አቅም መገንባት ይቻላት ዘንድ የአጭር፣ መካከለኛ እና የረዥም  ጊዜ እቅድ ነድፋ በመንቀሳቀስ ላይ መሆንዋን ዶክተር ሰለሞን ገልፀዋል።

በዚህም መሰረት በመጪዎቹ ሶስት ዓመታት የኮሙኒኬሽንና ፈጣን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ለማምጠቅ እንዲሁም የሳተላይት  ማምረቻና መገጣጠሚያ ጣቢያ ለመክፈት እቅድ መያዙንም ተናግረዋል።

በመጪዎቹ 15 ዓመታት ውስጥም የተለያየ ግልጋሎች የሚሰጡ አስር ሳተላይቶችን ወደህዋ ለማምጠቅ እቅድ እንዳለም እንዲሁ።

ሰሞኑን ወደህዋ የተላከችው  'ETRSS-1' ሳተላይት የሙከራ መረጃ ልውውጧን አጠናቃ ከቀናት በኋላ የተልዕኮ ስራዎችን እንደምትጀምር የሳተላይት ምርምር ልማት ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ ይልቃል ጫኔ  ተናግረዋል።

እስካሁን ባለው ሂደትም ከሳተላይቷ ጋር የተሳካ የሙከራ መረጃ ልውውጥ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀው ሳተላይቷ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከማዕከሉ እንድትተገብር የሚሰጣትን ተልዕኮ ማከናወን ትጀምራለች ብለዋል።

በዚህም ሳተላይቷ በቀን አስራ አራት ጊዜ መሬትን የምትዞር ሲሆን፤ እስካሁን ባለው ሂደትም በየእለቱ አራት ጊዜ መረጃ ወደ እንጦጦ ኦብዘራቫቶሪ ማዕከል እንደምትልክ በዚሁ ወቅት ተመልክቷል።

በዋናነትም ግብርናና የተፈጥሮ እንክብካቤ እንዲሁም የአየር ንብረት ሁኔታን በተመለከተ መረጃዎችን መላክ የምትጀምር ይሆናልም ነው ያሉት።

ሳተላይቷ የግብርና፣ የማዕድን፣ አካባቢ ጥበቃ፣ አየር ንብረት ለውጥና መሰል ጉዳዮችን የተመለከቱ መረጃዎችን ትሰጣለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም