በዱር እንስሳት ላይ እየተደረገ ያለውን ህገ ወጥ ዝውውር ለመግታት ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ ሊበጅለት ይገባል

72

ኢዜአ ታህሳስ 14 ቀን 2012 ዓ.ም በዱር እንስሳት ላይ እየተደረገ ያለውን ህገ ወጥ ዝውውር ለመግታት ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ ሊበጅለት እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ፡፡ የምክር ቤቱ የግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  የሆለታ የዱር እንስሳት ማቆያና የደን ልማት ክብካቤ ስራዎችን የመስክ ምልከታ አድርጓል።

ሆለታ ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ በ34  ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

የሆለታ ኮቴ የዱር እንስሳት መጠለያና የትምህርት ማዕከል ደግሞ በ77 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባ ነው፡፡

በማዕከሉ በአሁኑ ወቅት ከ160 በላይ በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የተያዙና ሌሎችም የተለያዩ የዱር እንስሳት ተጠልለው እንክብካቤ እየተደረገላቸው  ይገኛል።

በቋሚ ኮሚቴው የአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ንኡስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባዬ ገዛህኝ እንዳሉት የዱር እንስሳት ጥበቃ ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡

በዋናነትም የህግ ማዕቀፍ ረቆለት ተግባራዊ እንዲሆን የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጡት ይገባልም ነው ያሉት ሰብሳቢዋ፡፡

በዘርፉ ያሉ ሰራተኞችም ስለዱር እንስሳት በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው እንደሚገባና ጥበቃውም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው በመስክ ጉብኝቱ ላይ የተናገሩት ፡፡

በማዕከሉ የዱር እንስሳቶች አያያዝና እንክብካቤ እንዲሁም የደን ልማቱ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም በመስክ ምልከታው ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡

የመስክ ምልከታውን ዓላማ ሲገልጹም በህገ ወጥ መንገድ የዱር እንስሳቶች ላይ ጥቃት ይፈጸማል፤ እንስሳቶች ከተያዙ በኋላ ምን አይነት እንክብካቤ ይደረጋል? የደን ልማቱስ ምን ደረጃ ላይ ነው? የሚሉትን ቦታው ላይ በመገኘት ለማረጋገጥ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ በተለይም ተማሪዎች ስለ ዱር እንስሳት ያላቸው እውቀትና ግንዛቤ እንዲዳብር በማዕከሉ የዱር እንስሳቶቹን እንዲጎበኙ ማድረጉም የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

በማዕከሉ የዱር እንስሳትና ውጤቶቻቸው ዝውውርና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጳውሎስ በበኩላቸው በዱር እንስሳት ክብካቤ ዙሪያ የክልሎች ሚና ከፍተኛ ቢሆንም በተፈለገው ደረጃ ላይ አይደለም ብለዋል፡፡

በዘርፉ ላይ በቂ ግንዛቤ የሌላቸው የቁጥጥር ሰራተኞች መኖራቸውንም ነው የገለጹት፡፡

ክትትል በሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች በቂና ተከታታይነት ያለው ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ባለመሆኑም በህገ ወጦች ላይ እየተወሰነ ያለው ቅጣትና የህብረተሰቡ ተሳትፎ ዝቅተኛ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ዳይሬክተሩ እንዳሉት የዱር እንስሳት የመዘዋወሪያ መንገዶች በየጊዜው ተለዋዋጭና ውስብስብ መሆኑም ችግሩን እንዲባባስ አድርጓል ብለዋል።

ችግሩን ለመፍታትም የመገናኛ ብዙሃን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መስራት እነዲሁም ጠንካራ የቁጥጥር ስርአት መዘርጋት ይገባል ብለዋል።

የህብረተሰቡ ተሳትፎ ያለበትን አሰራር መዘርጋት እና በህገ ወጦች ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች አስተማሪና ሌሎችን ወደዚህ ተግባር እንዳይገቡ የሚያደርግ እንዲሆን መስራት ይገባልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም