የሐረር ነዋሪዎች በሞጣ የደረሰውን ጥቃት ተቃወሙ

50

 ኢዜአ ታህሳስ 13 / 2012 የሐረር ከተማ ነዋሪዎች በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ በእምነት ተቋማት ላይ የደረሰውን ጥቃት ዛሬ ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ተቃወሙ። ነዋሪዎቹ በሰላማዊ  ሰልፉ  ወቅት በኃይማኖት  ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት በማውገዝ እንደማይወክላቸው ገልጸዋል።

ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል ዶክተር ፈሪድ ዳዊት እንዳሉት ሰሞኑን በእምነት ተቋማት ላይ የደረሰው ጥቃት አሳዛኝ ነው፤ በመከባበርና በመፋቃቀር  የሀገሪቱን አንድነት መጠበቅ ይገባል።

መንግስት በእምነት ተቋማት ላይ እየተፈጸመ ያለውን  እኩይ ተግባር ተከታትሎ ህጋዊ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም አመልክተዋል።

አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት ችግሮቹን ከማባባስ እንዲቆጠቡም ጠይቀዋል።

ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ አቶ ተማም አባስ በበኩላቸው በእምነት ተቋማት  ላይ በደረሰው ጥቃት ማዘናቸውን በመግለጽ ድርጊቱን አውግዘዋል።

ይህ መጥፎ ተግባር የሚፈጽሙ አካላት ህዝበ ሙስሊሙንና ህዝበ ክርስቲያኑን የማይወክሉ    መሆናቸውን ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያ ለሁሉም ዜጋ የምትበቃ ሃገር በመሆኗ አንዱን ከአንዱ በማጋጨትና ወደ ሌላ ግጭት ለማምራት የሚደረገው ጉዞ በፍጥነት ሊቆም ይገባል ብለዋል።

በሞጣ ከተማ የእምነት ተቋማትና ግለሰብ ንብረት ላይ  የደረሰውን ጥቃት እንደሚቃወሙ  ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ  አቶ ዱላ ሚኖጂ ገልጸዋል።

ህዝቡን በጎሳ፣ በዘርና በኃይማኖት  በመከፋፈል  አንድነት እንዳይኖረው እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ በምንም  መልኩ ተቀባይነት እንደሌለውም ተናግረዋል።

ህብረሰተቡ የሰላም ፣የመቻቻል፣ የአንድነትና የፍቅር እሴቱን የሚሸረሽሩ ተግባራትን  መቃወምና መከላከል እንዳለበትም አመልክተዋል።

የኃይማኖት አባቶች ተከታዮቻቸውን ስለ አንድነት ፣ፍቅርና መቻቻል በየእምነት ተቋማት ጠንክረው  ማስተማር እንዳለባቸውም ሰልፈኞቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በከተማው በሚገኘው ራስ መኮንን አደባባይ የወጡት ሰልፈኞች የተቃውሞ ድምጻቸውን ካሰሙ  በኋላ  በሰላማዊ መንገድ ወደ የመጡበት መመለሳቸውን ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም