የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማግኘት መጉላላት እየገጠመን ነው … ተገልጋዮች

55

ኢዜአ፤ታህሳስ 13/2012 በአዲስ አበባ ከተማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፍጆታ ክፍያን ለመፈፀምና የአገልግሎት ችግር ሲያጋጥም ፈጣን መፍትሔ ስለማይሰጣቸው እንግልት እየገጠማቸው መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ ተገልጋዮች ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢሮ በበኩሉ ችግሩ የተከሰተው ደንበኞች በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መክፈል ባለመቻላቸው፣ በተሽከርካሪ እጥረት ና በመንገድ መዘጋጋት እንደሆነ ገልጿል።

ቢሮው ይሄን ይበል እንጂ ተገልጋዮች በተቀመጠላቸው የግዜ ሰሌዳ መሰረት የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያን ለመክፈል ወደ ተቋሙ በሚሄዱበት ጊዜ ከፍተኛ መጉላላትና እንግልት እየደረሰባቸው  መሆኑን ነው የሚገልጹት።

የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሰለሞን ይርጋ እንዳሉት የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያን ለመክፈል ስሄዱ ፈጣን አገልግሎት ስለማይሰጣቸው ረዥም ወረፋን በመጠበቅ ላላስፈላጊ የገንዘብና የጊዜ ብክነት እየዳረጋቸው ነው።

አገልግሎት ለማግኘት ወደ ሥፍራው ስሄዱም “የመክፈያ ደረሰኝ አልመጣም እየተባልን ረጃጅምና አሰልቺ ሰልፎችን ይዘን የምንጠባበቅበት ጊዜ ብዙ ነው“ ያሉት ደግሞ አቶ ማስረሻ አለሙ ናቸው፡፡

በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ብልሽት ሲደርስና የመብራት መጥፋት ችግር ሲያጋጥም በ905 የጥሪ ማዕከል ቢያመለክቱም አፋጣኝ ምላሽ እንደማይሰጣቸው የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ለምለም ተካልኝ ናቸው።

ለሚያነሱት ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ባለመሰጠቱ በተለይ ደግሞ የመስመሮችና የመብራት ምሰሶዎች ያረጁ በመሆናቸው በህይወታቸው ላይ ስጋት እንዳሳደረባቸዋል ነው ወይዘሮ ለምለም  የገለጹት።

የአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ በቀለ ክፍሌ እንዳሉት የደንበኞች የክፍያ ስርዓት በተለያዩ የጊዜ ሰሌዳ እና  የመክፈያ ጣቢዎች የተከፋፈለ ቢሆንም ደንበኞች ይህን መጠቀም ባለመቻላቸው በአንዳንድ አካባቢዎች ችግሩ አጋጥሟል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ደንበኞች እንዳይጉላሉ ዘርፉን በማዘመን የክፍያ ስርዓቱ ሙሉ በሙሉ በባንክ እንዲፈፀም ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

በመብራት መቆራረጥና በኤሌክትሪክ ምሰሶዎች መውደቅ ከደንበኞት የተነሱ ቅሬታዎች ትክክል መሆኑን ያነሱት አቶ በቀለ፤ የኤሌክትሪክ መስመሮችና ምሰሶዎች ለረጅም ዘመናት አገልግሎት የሰጡ በመሆናቸው በአዲስ ለመተካት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከደንበኞች የሚመጡ ጥሪዎች የሚስተናገዱት በተመዘገቡበት ቅደም ተከተል  በመሆኑ፣ የመንገድ መዘጋጋት እና በተሽከርካሪ እጥረት የሚጠየቁ አገልግሎቶች በፍጥነት እንዳይሰጡ አድርጓል ነው ያሉት።

የአገልግሎት ክፍያ ስርዓቱን ወደ ባንክ ለማዛወር የተጀመረው ሥራ እስኪጠናቀቅ ድረስ ደንበኞች በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የክፍያ ጣቢዎች በመሄድ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም