በትግራይ የሕጻናት የመቀንጨር ችግር እየሰፋ መምጣቱ ተጠቆመ

65
ኢዜአ ታህሳስ 13 / 2012 ዓ ም በትግራይ ክልል በሕጻናት ላይ የሚደርሰው የመቀንጨር ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መምጠቱን የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ። እናቶች ለእናቶች የተባለ አገር በቀል መንግስታዊ ያልሆነ ማህበር በህጻናት የአመጋገብ ስርአት ላይ ያተኮረ የማህበረሰብ አቀፍ የውይይት መድረክ በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ አካሂዷል። በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ የአመጋገብ ስርአት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ክፍለ ግርማይ እንዳሉት በክልሉ በህጻናት ላይ የሚደርሰው የመቀንጨር ችግር ከጊዜ ወደጊዜ እየሰፋ መጥቷል። ለእዚህም ቀደም ሲል በክልሉ 39 ከመቶ የነበረው የመቀንጨር አደጋ በአሁኑ ወቅት ወደ 41 ከመቶ ከፍ ማለቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል። ነፍሰጡር እናቶች በእርግዝና ወቅት የተመጣጠነ ምግብ አለመውሰድና ህጻናት ከተወለዱ በኋላ እስከ ሁለት ዓመታቸው የተመጣጠነ ምግብ በበቂ ሁኔ አለማግኘታቸው በህጻናት ላይ እየደረሰ ላለው የመቀንጨር ችግር ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን አስረድተዋል። ከምግብ አቅርቦት ችግር ባሻገር የአስተሳሰብና የግንዛቤ እጥረት የተመጣጠነ ምግብ ላለመውሰድ የሚጠቀስ ምክንያት መሆኑንም ነው አቶ ክፍለ ያመለከቱት። በገጠር የሚኖሩ እናቶች በእርግዝና ጊዜያቸው የተመጣጠነ ምግብ እንዲወስዱ እናቶች ለእናቶች የተባለ ማህበር የግንዛቤ ትምህርት የሚሰጡ ሰዎችን በማስልጠን ወደሥራ ማስገባቱ የሚበረታታ መሆኑንም ተናግረዋል። የእናቶች ለእናቶች ማህበር ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ አስመላሽ በበኩላቸው ማህበሩ በህጸናት ላይ ጎልቶ እየታየ የመጣውን የመቀንጨር ችግር ለመቀነስ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይ በገጠር የሚኖሩ እናቶች በእርግዝና ጊዜያቸው የተመጣጠነ ምግብ እንዲመገቡ የአቻ ለአቻ ትምህርት የሚሰጡ ሰዎችን በማስለጠን ወደ ሥራ ማስገባቱን ተናግረዋል። ባለፉት ሦስት ዓመታት ከሁለት ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ማሰልጠኑንም ነው አቶ አሸናፊ የገለጹት። የውይይቱ ተሳታፊ ቄስ ተክላይ ካህሳይ በሰጡት አስተያየት እናቶች በእርግዝና ጊዜያቸው በእምነታቸው ምክንያት የጾም እና የፍስግ በሚል ሳይለዩ እንዲመገቡ ምክር እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል። በእናቶች ለእናቶች ማህበር በተመጣጠነ ምግብ አዘገጃጀት ላይ ስልጠና ማግኘታቸውን የተናገሩት ወይዘሮ ምጽላል አባይ በበኩላቸው፣ በአካባቢያቸው የአምስት እርጉዝ እናቶችን የአመጋገብ ስርአት ከመከታተል ባለፈ በተመጣጠነ ምግብ አዘገጃጀት ላይ ትምህርት እየሰጧቸው መሆኑን ተናግረዋል። የሚያደርጉትን ክትትልና የሚሰጡትን ምክር እናቶች ወልደው ልጆቻቸው ሁለት ዓመት እስኪሞላ ድረስ  እንደሚቀጥሉበት ገልጸዋል። እናቶች ለእናቶች ማህበር ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በ6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወጪ የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በማከናወን ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተጠቃሚ ማድረጉ ታውቋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም