በኢትዮጵያና ቻይና ባህልና ትብብር ማጠናከር ላይ ያተኮረ መጽሃፍ ተመረቀ

67

ኢዜአ ታህሳስ 13/2012 በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ባህልና ትብብር ማጠናከር ላይ ትኩረቱን ያደረገ መጽሃፍ ዛሬ በአዲስ አበባ በይፋ ተመርቋል። መጽሃፉ የተዘጋጀው 'ሴንተር ፎር ዳያሎግ፣ ሪሰርች፣ኤንድ ኮኦፕሬሽን' እና 'ሴንተር ፎር ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ኤቲክስ' በተባሉ ማዕከላት በጥምረት መሆኑም ተገልጿል።

በመጽሃፉ ይፋዊ የማስተዋወቂያ መርሃ ግብር ላይ 'ሴንተር ፎር ዳያሎግ፣ ሪሰርች፣ኤንድ ኮኦፕሬሽን' የቦርድ አባል የሆኑት አምባሳደር ተቀዳ ዓለሙ እንደተናገሩት፤ "መጽሃፉ በቻይና እና ኢትዮጵያ ትብብር ላይ ያሉትን መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ከአድልኦ ነጻ በሆነ መንገድ በጥልቀት የሚዳስስ ነው"።

በተጨማሪም አገራቱን ግንኙነት ለማሳደግ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ማድረጉንም ተናግረዋል።

ይህም የአገራቱን ትብብር ለማጠናከርና ዘላቂ ለማድረግ ጠቃሚ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ማዕከሉ ለኢትዮጵያ ብሎም በአጠቃላይ ለአፍሪካ ቀንድ አገራት ልማት ስራዎች ጠቃሚ የሆኑ የጥናትና የምርምር ስራዎችን የሚደግፍ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ማዕከሉ የቻይና-ኢትዮጵያ እንዲሁም የቻይና አፍሪካ ትብብር የሚያጠናክሩ መረጃዎችን መሰረት ያደረጉ ጥናቶችን እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በበርካታ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ተሰማርቶ የሚገኘው የቻይናው 'ሲ ሲ ኢ ሲ' የኮንስትራክሽን ኩባንያ ምክትል ስራ አስኪያጅ ዛንግ ዜንሄ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ስራ ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች መፅሃፉ እንደ መመሪያና ማጣቀሻ የሚያገለግል ነው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም የሁለቱን አገራት ትብብር እንደሚያጠናክርም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም