ኢትዮጵያ በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ረዥም ርቀት እንድትጓዝ ከታች ከትምህርት ቤት ጀምሮ መሰራት አለበት --- ምክር ቤቱ

70
ኢዜአ ታህሳስ 13/2012 ኢትዮጵያ በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ረዥም ርቀት እንድትጓዝ ከታች ከትምህርት ቤት ጀምር መሰራት እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ። በምክር ቤቱ የሰው ሃብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ ማዕከልን ዛሬ ጎብኝተዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ በስፍራው በመገኘት ኢትዮጵያ ከሶስት ቀናት በፊት ያመጠቀቻት ሳተላይት ስላለችበት ሁኔታ ለአባላቱ ገለጻ አድርገውላቸዋል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ውይዘሮ እምዬ ቢተው በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የጉብኝቱ ዋነኛ ዓለማ ሳተላይቷ በምን ሁኔታ ውስጥ እንድምትገኝ ለመመልከት መሆኑን ገልጸው፤ በተመለከቱት ነገር መደሰታቸውን  አብራርተዋል። ቋሚ ኮሚቴው በቀጣይ የሚጠበቅበትን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም ተናግረዋል። የህዋ ሳይንስ ዘርፍ እድገት ጊዜ የሚፈልግ መሆኑን የተናገሩት ሰብሳቢዋ፤ በመሆኑም መንግስት የዘርፉን ተረካቢ ትውልድ ከወዲሁ ማዘጋጀት አለበት ብለዋል። ዘርፉን በሚመለከት ከታች ከትምህርት ቤት ጀምሮ ግንዛቤ ከማስጨበጥና በካሪኩለም አካቶ ገቢራዊ እስከማድረግ  ሊታሰብ እንደሚገባም አሳስበዋል። በቋሚ ኮሚቴው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ወንድሙ ገላጋይ በበኩላቸው አሁን ላይ በዘርፉ የተሰማሩ አብዛኞቹ ባለሙያዎች ወጣቶች መሆናቸው የሚበረታታ ጅምር መሆኑን ገልጸዋል። በቀጣይም ወጣቶችን በማሰልጠን ተቋሙን የሚቀላቀሉበት መንግድ በስፋት ሊመቻችላቸው እንደሚገባ በመጠቆም። የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ኢንስቲትዩት ከትምህርት ተቋማት በተጨማሪ ከሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር ያለውን ትስስር ማጥበቅ እንደሚገባውም ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲዎች የስፔስ ሳይንስ ትምህርት ክፍል አቋቁመው ለዘርፉ ሰኬት በኃላፊነት መስራት አለባቸው ያሉት ደግሞ የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ንብረት ፈንታሁን ናቸው። በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ የሚያከናውናቸውን ተግባራትና ያጋጠሙትን እክሎች በየጊዜው ለህዝብ ይፋ ማድረግ እንዳለበትም አውስተዋል። ይህም ግልጸኝነትን ከመፍጠሩ በላይ ዜጎች በተለያዩ አካላት በሚሰራጩ የሀሰት መረጃዎች እንዳይደናገሩ ያግዛልም ነው ያሉት።     'ETRSS-1' ቻይና ከሚገኝ ማምጠቂያ ማዕከል ነው ዓርብ ማለዳው ላይ ወደ ህዋ የመጠቀችው።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም