ከጮቄ ተራራ በየዓመቱ 600 ሄክታር መሬት ለቤት መስሪያና ለእርሻ አገልግሎት እየዋለ ነው

85
ኢዜአ ታህሳስ 13/2012  በምስራቅ ጎጃም ዞን ለሚገኘው የጮቄ ተራራ ተገቢ ጥበቃ ባለመደረጉ በየዓመቱ 600 ሄክታር የተራራው መሬት በወረራ ለመኖሪያ ቤት መስሪያና ለእርሻ አገልግሎት እየዋለ መሆኑ ተገለጸ። የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር በበኩሉ የተራራውን 6ሺህ 24 ሄክታር መሬት በማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ስፍራ በመከለል ከአደጋ የመጠበቅና መልሶ የማልማት ሥራ መጀመሩን አስታውቋል። በጮቄ ተራራ የማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ስፋራ አያያዝና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በባህር ዳር ከተማ ውይይት ተካሂዷል። በውይይት መድረኩ ላይ እንደተገለጸው የጮቄ ተራራ በውስጡ 23 ወንዞች፣ 186 ምንጮች፣ 41 ውሃ አዘል መሬት እንዲሁም የተለያዩ አይነት የእጽዋት፣ አዕዋፍና አጥቢ እንስስትን አካቶ የያዘ ነው። በአማራ ክልል አካባቢ ጥበቃ፣ ደንናዱር እንስሳት ጥበቃ ልማት ባለስልጣን የዱር እንስሳትና መኖሪያቸው ጥናትና ምርምር ባለሙያ አቶ በቀለ ዘሪሁን፣ የጮቄ የተራራ ቀደም ሲል ጥቅጥቅ ያለ ደን ያለውና ብዝሃ ህይወቱም የተጠበቀ እንደነበር ተናግረዋል። ባለሙያው እንዳሉት የጮቄ ተራራ 16 ሺህ 300 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ቢሆንም በአሁኑ ወቅት አብዛኛው መሬት በአካባቢው በሚኖሩ ሰዎች ለጉዳት ተጋልጧል። የተራራው አካል የሆነውን መሬት በህገወጥ መንገድ በመውረር ለቤት መስሪያና ለእርሻ አገልግሎት ጥቅም ላይ እንዲውል እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። "በተራራው ዙሪያ ከ80 ሺህ በላይ አባውራዎች ይኖራሉ" ያሉት ባለሙያው የከፋ የደን ምንጣሮ እየተከናወነ መሆኑንም አቶ በቀለ አብራርተዋል። ተራራው ለቤት እንስሳት ልቅ ግጦሽ እየወለ መሆኑን ጠቁመው፣ በእነዚህና መሰል ችግሮች በየዓመቱ ከ600 ሄክታር በላይ የተራራው ክፍል ለጉዳት እየተጋለጠ መሆኑን ተናግረዋል። በእዚህም ተራራው የከፋ የብዝሃ ሕይወት ውድመት እየደረሰበት መሆኑ ነው ያመለከቱት። እንደ አቶ በቀለ ገለጻ ለችግሩ በዘላቂነት እልባት ለመስጠት መንግስት ህብረተሰቡን ባሳተፈ መንገድ የወሰን ማስከበርና መልሶ ማልማት ስራ ጀምሯል። የምስራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ኑርልኝ ብርሃኑ በበኩላቸው "የጮቄ ተራራ እየደረሰበት ካለው ጉዳት ለመታደግ ስራዎች ተጀምረዋል" ብለዋል። ጮቄን የመጠበቅ፣ የማልማትና የአካባቢው ማህበረሰብ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ 6 ሺህ 24 ሄክታር የተራራው መሬት በማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ስፍራ በመከለል የማልማት ሥራዎች ተጀምሯል። "በተለይም ወጣቶች ተደራጅተው በንብ ማነብ፣ በዶሮ እርባታ፣ በደን ልማትና መሰል ሥራዎች እንዲሳተፉ በማድረግ በጮቄ ተራራ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ እየሰተራ ነው" ብለዋል። በጮቄ ተራራ አሁንም ልቅ ግጦሽ፣ የደን ውድመት፣ የእርሻ መሬት ማስፋፋት፣ ህገ ወጥ የቤት ግንባታና መሰል ችግሮች አለመቆማቸውን ገልጸው፣ ህብረተሰቡን በማወያየት ችግሩን ለመፍተት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። በብዝሃ ሕይወትና ስነ ምህዳር ጥበቃ የህብረተሰቡ ሚና ማደግ እንዳለበት የገለጹት ደግሞ በፌደራል አካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የብዝሃ ሕይወት ማካተቻና ማትጊያ ፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባባሪ አቶ አብዴታ ደበላ  ናቸው። "ኢትዮጵያ ከፍተኛ የብዝሃ ህይወት ያላት አገር ብትሆንም በአያያዝና አጠቃቀም ጉድለት ለውድመት ተጋልጧል" ብለዋል። ይህን ለመከላከልም ህብረተሰቡን አሳታፊ የሚያደርጉ አሰራሮችን ለመዘርጋትና አካታች ፖሊሲ እንዲወጣ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። በብዝሃ ሕይወት ማካተቻና ማትጊያ ፕሮጀክት ከጮቄ በተጨማሪ በአርባ ምንጭ ጉልፎ ተፋሰስ፣ በምስራቅ ወለጋ ዲጋ ደን እንዲሁም በሶማሌ ክልል ሃደው የግጦሽ ስፍራ የጥበቃና እንክብካቤ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል። በውይይቱ ከምስራቅ ጎጃም ዞን አምስት ወረዳዎች፣ ከፌደራልና ከክልል የተውጣጡ አማራሮች ተገኝተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም