በኃይማኖት ሽፋን የህዝቡ ጠንካራ አንድነት ማላላት እንደማይቻል የኃይማኖት አባቶች ገለጹ

70
ኢዜአ ታህሳስ 13/2012 ኃይማኖትን ሽፋን በማደረግ በሚፈጸም ጥፋት የህዝቡን የቀደመ ጠንካራ አንድነቱን ማላላት እንደማይቻል የኃይማኖት አባቶች ገለጹ። በሞጣ ከተማ በደረሰው ጉዳትና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ  የኃይማኖት አባቶችና የመንግስት አመራሮች ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር  ዛሬ ተወያይተዋል። በውይይቱ ወቅት የባህር ዳር ሃገረ ስብከትና ቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ አብረሃም እንዳሉት የኢትዮጰያ ክርስቲያንና ሙስሊም ህዝብ በኃይማኖት የሚጣላ ሳይሆን አንዱ የአንዱን ቤተ እምነት ለመገንባት በገንዘብና በጉልበቱ በማገዝ ተባብሮ የኖረ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለግል ጥቅም ሲባል ኢትዮጵያን ከፋፍሎ ለመግዛት የተደረገው ጥረት አልሳካ ሲል በኃይማኖት ስበብ ህዝቡን ለመከፋፈል ቀን ከሌት ታስቦበት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ሰሞኑን የተፈጠረው ችግርም  ህዝቡን ለበለጠ አንድነትና ፍቅር እንዲሁም መተሳሰብ የሚያነሳሳው እንጂ አንዱ ባንዱ ላይ በጠብ አጫሪነት እንዲቆም አያደርገውም። "ይህን እውነታ ለማረጋገጥም ህዝቡ  በፍጥነት ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተ እምነቶች መልሶ በመገንባትና ንብረት የወደመባቸውን ወገኖች በመተካት መካስ "ይገባል ብለዋል። "እንደ ሃገር ኢትዮጵያዊያንን በኃይማኖት ስበብ ለመከፋፈልና የእርስ በእርስ ግጭት ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ ነው "ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የኡላማዎች ምክር ቤት ዋና ፀሃፊ ቃሲም ሙሃመድ ታጁድ ናቸው። በኃይማኖት ሽፋን የኢትዮጵያን ህዝብ መከፋፈልም ሆነ ወደ ግጭት ውስጥ ማስገባት ፈጽሞ እንደማይቻልም ገልጸዋል። በተለይም የአማራ ህዝብ በተነገረው ሳይሆን የተነገረውን  መርመሮና አገናዝቦ ለመፍትሄ የሚተጋ አስተዋይ ህዝብ መሆኑን አመልክተዋል። ህዝቡ በእንደዚህ አይነት መሰረተ ቢስ ጉዳዮች የቀደመ አንድነቱን የሚሸረሽር ሳይሆን የበለጠ በሚያቀራርቡና በሚያዋድዱ ተግባራት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል። የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ አብረሃም አያሌው በበኩላቸው እንደተናገሩት  የአማራን ህዝብ ወደ ግጭት ለማስገባት እየተደረገ ያለው ሴራ  የማይሳካ ነው። የአሁኑ ክስተትም የህዝብን  አንድነት ይበልጥ  የሚያጠናክርና ለጠላቶች የማይበገር መሆኑን በማያደግም ሆኔታ ማሳያ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። "በተፈጠረው ድንገተኛ ችግር ጉዳት የደረሰባቸው ቤተ እምነቶችም ሆነ የግለሰቦች ንብረት መልሶ ለመተካትና ለማቋቋምም አብይ ኮሚቴ በማዋቀር የመለየት ስራ ለመጀመር ዝግጅት ተደርጓል" ብለዋል። " የአማራ ህዝብ በትንንሽ ጉዳዮች ተሰናክሎ የማይወድቅ ጠንካር ህዝብ ነው " ያሉት ደግሞ  የክልሉ አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘው ተሻገር ናቸው። የክልሉን ገፅታ ለማበላሽት የሚጥሩ አካላትን የሴራ እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ በማክሸፍ  አለኝታ መሆኑን በተጨባጭ ማሳየት እንደቻለም ጠቅሰዋል። ባለፉት ጊዜያት የተከሰቱ ችግሮችን ፈጥኖ በማስተካከል ክልሉን አስተማማኝ የሰላም ቀጠና ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፤ ህዝብን ለማጋጫት የሚጥሩ አካላትንም በጥንቃቄ በመለየት ለህግ እየቀረቡ መሆናቸውንም አስታውቀዋል። በሞጣ አካባቢ በተከሰተው ድንገተኛ ችግርም የክልሉ መንግስት ፈጥኖ በመድረስ ወደ ቀደመ ሰላሙ መመለስ መቻሉን ጠቅሰው፤ በዚህ ድርጊት የተሳተፉ አካላትን ከህዝቡ ጋር በመሆን ለይቶ ለህግ ለማቅረብ  እየተሰራ መሆኑንም አመለክተዋል። በውይይቱ በየደረጃው ያሉ የአመራር አካላት ፣ የኃይማኖት አባቶችና  ከሞጣ ከተማ የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም