የድሬደዳዋን ሰላም ለማስጠበቅ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ

54
ኢዜአ ታህሳስ 13/2012፡- በድሬዳዋ አስተዳደር ሰላምን ለማስጠበቅና ልማትን ለማጎልበት ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ። ካለፈው ጳጉሜ ጀምሮ በድሬዳዋ ችግር በተፈጠረባቸው 44 መንደሮች እርቀ-ሰላም ለማመቻቸት ታዋቂ ሰዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የተካተቱበት ኮሚቴ አባላትና ሌሎችም የህብረሰተብ ክፍሎች ከአስተዳደሩ አመራሮችና ከፍትህ አካላት ጋር ተወያይተዋል፡፡ በዚሁ ወቅት በተለይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች ፣ አባገዳዎችና ዑጋዞች የተሰጣቸውን ሰማያዊና ምድራዊ ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት እጅ ለእጅ ተያይዘው የተጣሉትን ለማስታረቅ እንደሚተጉ ተናግረዋል። ህዝቡን አስተባብረው በግጭት የተጎዱትን ለመካስ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡ በተቀናጀ መንገድ ሰላም በማስፈን በፍቅርና በአንድነት በድሬደዋ ብሎም በሀገር አስተማማኝ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ  ገልጸዋል። በውይይት የተሣተፉት አቶ ሙክታር ቃሲም “ሰላም የማይተመን ትልቅ ዋጋ አለው፤ካለፈው ግጭት ተምረናል፤ ሰላምን ከራሳችን በመጀመር የተጣለብንን ተልዕኮ እንወጣለን “ብለዋል፡፡ ቀሲስ አፈወርቅ አስፋው ሁሉም እምነቶች በየቤተ-እምነቱ ሰላምና ፍቅርን ያስተምራሉ፤ ይህንኑ ሰማያዊና ምድራዊ ኃላፊነት በመወጣት በህዝቦች መካከል ሰላም ፍቅር እንዲጠናከር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ አንዴ በብሔር ፣ሌላ ጊዜ በኃይማኖት ስም ርካሽ የፖለቲካ አስተሳሰብና ፍላጎታቸውን ለማሳካት ጥልና ብጥብጥ የሚፈጥሩ አካላት በተቀናጀ መንገድ ማውገዝና ለህግ ማቅርብ እንደሚገባም አመልክተዋል። አቶ ሸምሸዲን ሙሣ በበኩላቸው ሁሉም የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት የተጀመረውን የእርቀ ሰላም ስራ ማሳካት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የፖለቲካው አመራር የራሱን ፣ ሰራተኞችም የራሳቸው ኃላፊነት፣ የእምነት አባቶችም ተልዕኳቸውን ከተወጡ ጥልና ሁከት በድሬዳዋ ቦታ እንደማይኖረው ተናግረዋል። “ጥላቻን ከውስጣችን በማውጣት በቁጭት፣ በፍቅር፣ በአንድነት በመረባረብ የዱሮዋን የፍቅርና የሰላም ከተማ - ድሬዳዋን ለመመለስ እንረባረባለን” ያሉት ደግሞ ሐጂ መሐመድ ጅብሪል ተስፋዬ ናቸው። የሀገር ሽማግሌው አቶ መላኩ ዘመነ በሁከት ወቅት ለተጎዱ ዜጎች አስተዳደሩ እንዳፅናናው ሁሉ ካለው ውስን በጀትም ቢሆን ቢደግፋቸው ለእርቀ-ሰላሙ ተልዕኮ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል። “እኛም ከራሳችን ጀምረን ህዝብንና ባለሃብቱን አስተባብረን የሚደገፉበት መንገድ እንፈጥራለን “ብለዋል፡፡ የሰላም መሠረቱ ቤተሰብ በመሆኑ ሁሉም ልጆቹን በአግባቡ ከተቆጣጠረ ሰላም የማይሰፍንበት ምክንያት እንደማይኖር የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ አሚና ዑመር ናቸው፡፡ ወጣት መሃመድ ገመቹ በሰጠው አስተያየት በድሬዳዋ ተፈጥሮ የነበረው ብጥብጥ ውስጥ እጃቸው ያለበት አመራር በህግ ሊጠየቁ ፤በድርጊት ውስጥ የተሳተፉትም ህዝብን ይቅርታ ሊጠይቁ እንደሚገባ አመልክቷል። “በሰባተኛ አካባቢ የጀመርነውን የእርቅ ተግባር ለማጠናከር ዝግጁ ነን፤ መንግስትም የህግ የበላይነትን ሊያረጋግጥ ይገባል “ብለዋል፡፡ ውይይቱን የመሩት በምከትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር በድሬዳዋ ተከስቶ በነበረው ችግር ውስጥ የተጠረጠሩ በመያዝ የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት በተቀናጀ መንገድ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል፡፡ “ህግ ከማስከበሩ በተጓዳኝ ከተያዘው ሣምንት ጀምሮ እስከ ታህሳስ 25 ድረስ በየመንደሩ የሚከናወነው የእርቅ ሥራ የተጀመረውን አስተማማኝ ሰላም የማስፈንና ልማትን የማስቀጠል ተግባራት ያጠናክራል “ብለዋል፡፡ ለሚከናወኑ ተግባራት አስተዳደሩ ባለው አቅም ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም