ሴቶች ዘመናዊ የማምረቻ መሳሪያዎችን በሊዝ መግዛት እንዲችሉ የሚያደርግ ፕሮጀክት ስምምነት ተፈረመ

144
ኢዜአ ታህሳስ 12/2012 ሴቶች የምርት አገልግሎቶችን በጥራትና በብዛት ለማምረትና ለገበያ ማቅረብ እንዲችሉ ዘመናዊ የማምረቻ መሳሪያዎችና ቴክኖሎጂዎችን በሊዝ መግዛት የሚያስችላቸው አሰራር የሚተገርበት የፕሮጀክት ስምምነት ተፈረመ። ፕሮጀክቱ የሴቶች ኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ፕሮጀክት ደንበኞች ምርትና አገልግሎቶቻቸውን በጥራትና በብዛት ለማምረትና ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችላቸውን ዘመናዊ የማምረቻ መሳሪያዎችና ቴክኖሎጂዎችን በሊዝ መግዛት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል። ይህም በፌዴራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ፣ በአዲስ የካፒታል እቃ ፋይናንስ ንግድ ስራ  እና በኦሮሚያ የካፒታል እቃ ፋይናንስ ንግድ ስራ አክስዮን ማህበሮች መካከል ነው የተፈጸመው። ፕሮጀክቱ የሴቶች ኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ፕሮጀክት በምርት፣ በአገልግሎትና በምርት ስራ ለተሰማሩ ሴት ኢንተርፕርነሮች የስልጠናና የብድር አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል። የዚህም ፕሮጀክት የብድር ውል ስራ በኢትዮጵያ መንግስት እና በዓለም ባንክ መካከል እ.አ.አ ሰኔ 12 ቀን 2012 የተጀመረ ነው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮም ከ11 የመንግስት የስልጠና ተቋማት እና ከስምንት አነስተኛ የብድር ተቋማት ጋር እንዲሁም ከ45 የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች ጋር በመቀናጀት የአነስተኛና የመካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ባለቤቶችን ስልጠናና ብድር ተደራሽ ሲያደርግ መቆየቱም ተጠቁሟል። የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ዮሃንስ ዘላለም ስምምነቱ ሲፈረም እንደገለጹት፤ ነጋዴውን ማህበረሰብ፣ አገልግሎት ሰጪ እና አምራች ሴቶችን በስልጠናና በብድር አገልግሎት በተጨማሪ ስምንት ከተሞች ለማስፋት የቅድመ ዝግጅት ስራ ተጠናቋል። ለዚሀም የ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የብድር አገልግሎት የተመቻቸ ሲሆን ስራውም በዚህ አመት የሚጀመር መሆኑንም ገልጸዋል። የአዲስ የካፒታል እቃ ፋይናንስ ንግድ ስራ ማህበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ መሳይ እንሰጌ በበኩላቸው የሴቶችን ሁለንተናዊ አቅም ለማጎልበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማስፋት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል። የኦሮሚያ ካፒታል እቃዎች ፋይናንስ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ገለታ ''ፕሮጀክቱ የሴቶችን ተጠቃሚነት ከማሳደግ አንጻር እስካሁን ከሰራናቸው ስራዎች በይበልጥ እንድንተጋ ያደርገናል'' ሲሉ ተናግረዋል። ይህ ፕሮጀክት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ እስካሁን 20 ሺህ 569 ኢንተርፕርነሮች የሙያ ስልጠና አግኝተዋል። 13 ሺ 312 ሴት ኢንተርፕርነሮች ደግሞ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ከፌዴራል ከተሞች የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም