ሕብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጎን በመቆም ሰላሙን እንዲጠብቅ ጥሪ ቀረበ

68
ኢዜአ ታህሳስ 12 / 2012 ሕብረተሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከጸጥታ ኃይሎች ጎን በመቆም ሠላሙን እንዲጠብቅ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ጥሪ አቀረቡ። በባምባሲ ፖሊስ ማሰልጠኛ ስልጠናቸውን የተከታታሉ ከ1 ሺህ በላይ ሚኒሻዎች ዛሬ ተመርቀዋል፡፡ አቶ አሻድሊ ሃሰን በእዚህ ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ ያለውን ሠላም ዘላቂ በማድረግ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡ በክልሉ አሁንም አልፎ አልፎ የተወሰኑ የጸጥታ ችግሮች እንደሚታዩ የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ የጸጥታ ኃይሎችን አቅም ከማጠናከር ጀምሮ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ የአካባቢን ሠላም ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ሚና የማይተካ መሆኑን ጠቁመው፣ የክልሉ ነዋሪዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የአካባቢያቸውን ሰላም እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በየቀበሌው የሚገኙ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊሶች እና የሚኒሻ አባላት በሚያጋጥሟቸው ችግሮ በቅርበት ከሚገኙ የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመነጋገር እንዲፈቱም አስገንዝበዋል፡፡ አቶ አሻድሊ እንዳሉት የጸጥታ ኃይሎችን አቅም በማጠናከር የሚደረገው ጥረት በቀጣይም አቅም በፈቀደ መጠን ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የፖሊስ ማሰልጠኛው ማዕከል ኃላፊ ኮማደር ዳምጠው ማሞ በበኩላቸው ዛሬ የተመረቁት 1ሺህ 5 የሚሊሻ አባላት በፈቃደኝነት የተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ "ሰልጥነው ለምረቃ የበቁት ሚሊሻዎች በህገ-መንግስት እና በሰብዓዊ መብት፣ በጦር መሳሪያ አያያዝ፣ በስምግባር፣ በወንጀል መከላከልና የታጠቁ ኃይሎችን መከላከል ጨምሮ ለአንድ ወር የተለያዩ ወታደራዊ ስልጠናዎችን ወስደዋል" ብለዋል፡፡ ሰልጣኞቹ በበኩላቸው ባገኙት ስልጣና በመታዝ ዘር፣ ሃይማኖትና ሌሎችንም ልዩነቶች ሳያደርጉ የህብረተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅ ቃል ገብተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም