የሃይማኖት ብዝሃነት ከግጭትና ስጋት ይልቅ የሰላምና የአንድነት መሰረት ነው...ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሒም

78
ኢዜአ ታህሳስ 12/2012.. የሃገራችን የሃይማኖት ብዝሃነት የግጭትና የስጋት ምንጭ ሳይሆን የሰላም፣ የመቻቻልና የአንድነት መሰረት መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤር አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሒም ገለጹ። ምክር ቤቱ ከፌዴራልና ከክልል የሴቶችና የወጣት አደረጃጀቶች እንዲሁም መዋቅሮች ጋር በፌዴራሊዝምና በሀገር ግንባታ ዙሪያ ዛሬ በአዳማ ከተማ መክሯል። በመድረኩ ላይ አፈ-ጉባኤዋ እንዳሉት አንዳንድ አካላት ብሄርን ከብሄርና ሃይማኖትን ከሃይማኖት በማጋጨት ሰላምን ለማወክ የሚያደርጉት ጥረት አይሳካም። "እነዚህ ኣካላት የማንንም ብሄርና ሃይማኖት አይወክሉም" ያሉት አፈ ጉባኤዋ የሃይማኖት ብዝሃነት የግጭትና የስጋት ምንጭ ሳይሆን የሰላም ፣የመቻቻልና የአንድነት መሰረት መሆኑን ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅት የሃይማኖትና የብሄር እኩልነት ወደ ኋላ በማይቀለበስበት ደረጃ መድረሱን ገልጸው ይሄን በመጣስ የሚከናወን አፀያፊ ተግባርን ሁሉም ሊያወግዘው እንደሚገባ አሳስበዋል። የህዝቦች ሰላምና ዲሞክራሲያዊ ኣንድነት እንዲጠናከር መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸው ለዚህም የወጣቶችና የሴቶች ሚና የላቀ በመሆኑ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። የሴቶች፣ወጣቶችና ሕፃናት ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ጸጋይ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ብሄርና ሃይማኖትን ለመከፋፈል የሚደረግ እንቅስቃሴን ወጣቶችና ሴቶች በጋራ ሊታገሉት እንደሚገባ ገልጸዋል። በተለይ ወጣቶች ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ድርጊቶችን አጥብቀው በመታገል የአካባቢያቸውን ሠላም እንዲያስጠብቁ አሳስበዋል። ከተሳታፊዎች መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ ኃይለሰማዕት መርሃጥበብ መድረኩ ወቅቱን የጠበቀና ተገቢውን ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚሰራበት መሆኑን ተናግሯል። "ሰላምን በህግ ብቻ ከማስከበር ባለፈ በማህብረሰብ መስተጋብርና ሥነ-ምግባር እያነጹ መጓዝ መፍትሄ ያመጣል"ብሏል። ሴቶችንና ወጣቶችን በሚፈለገው ደረጃ ያሳተፈ በቂ እንቅስቃሴ ባለመሰራቱ በሰላም ግንባታ ላይ መሰረታዊ ለውጥ እንዳይመጣ እንቅፋት መሆኑን የተናገረው ደግሞ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሙሀዲን ናስር ነው። "ከለውጡ ጋር የሚስማማ ጠንካራ መዋቅር በመፍጠርና በመዘርጋት ከመንግስት ጋር ተባብረው የሚሰሩበት ሁኔታ ሊመቻች ያስፈልጋልም" ብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም