የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ድሬዳዋን ምቹ የመኖሪያ ስፍራ ማድረግ ይገባል ተባለ

65
ኢዜአ ታህሳስ 12/ 2012 ---የተተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ በማሳደግ ድሬዳዋን ጽዱና ውብ የመኖሪያ ሥፍራ የማድረግ ራዕይን ለማሳካት መረባረብ እንደሚገባ የድሬዳዋ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ አስታወቀ። ከመቶ በላይ የሚሆኑ የቢሮው ሠራተኞች የፀረ- ሙስና ቀንን ምክንያት በማድረግ ‹‹በአረንጓዴ አሻራ›› ቀን የተከሏቸውን ችግኞች ትናንት ውሃ አጠጥተዋል፡፡ ችግኞችን በመንከባከቡ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተሳተፉት የቢሮው ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ ለኢዜአ እንደገለጹት ችግኞችን መንከባከብና ማሳደግ ለድሬዳዋ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ የድሬዳዋ ሞቃታማ አየርን ለመለወጥ፣ የጎርፍ ተጋላጭነቷን ለመቀነስና የከርሰ ምድር የመጠጥ ውሃ እንዲጎለብት ችግኞችን መንከባከብና ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ እንደ አቶ ሱልጣን ገለጻ በአረንጓዴ አሻራ ቀን ብቻ 258 ሺህ፤ በክረምቱ ሁለት ወራት ደግሞ 790 ሺህ ችግኞች በገጠርና በከተማ ተተክለዋል። "ብዙ ሃብት፣ እውቀትና ጉልበት የፈሰሰባቸውን ችግኞች ማምከንና አለመንከባከብ ከሙስና ተግባር ተለይቶ አይታይም " ብለዋል፡፡ በመሆኑም የድሬዳዋ ነዋሪዎች የተከሏቸውን ችግኞች በአግባቡ በመንከባከብ ድሬዳዋን ጽዱና ምቹ የመኖሪያ ሥፍራ የማድረጉ ተግባር ላይ እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በቢሮው የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል ባለሙያ ወይዘሮ ወርቅአፈራው ታዬ ለነዋሪውም ሆነ ለተተኪው ትውልድ አርአያ የመሆን ዓላማ ለማሳካት የፀረ-ሙስና ቀንን በችግኞች መንከባከብ ማክበራቸውን ተናግረዋል፡፡ "ምንግዜም ያለንን ውስን ሃብትና በጀት አገርና አካባቢን ለመለወጥና ለማሳደግ እንጂ ለብክነት መዳረግ አይገባም" ያሉት ባለሙያዋ፣ ማህበረሰቡም የሙስና ተግባራትን በተቀናጀ መንገድ መከላከል እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ "የተከልኳቸውን ችግኞች እንደልጅ የመንከባከብ ኃላፊነት እንዳለብኝ ይሰማኛል" ያለችው ደግሞ የቢሮው ሠራተኛ ወጣት ትዕግስት በለጠ ናት፡፡ "ሁሉም በየደረጃው የተከለውን ችግኝ ተንከባክቦ በማሳደግ ዛፍ ማድረግ ከቻለ ድሬዳዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ የመኖሪያ ከተማ ትሆናለች" ብላለች፡፡ የቢሮው አመራር ወይዘሮ ሰአዳ አዋሌ በበኩላቸው ለሥራ ወደ ገጠር በሚሄዱበት ወቅት አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ሃብትን ከመንከባከብ ጎን ለጎን የተከላቸውን ችግኞች እንዲያሳድግ በማስተማር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዛሬ ችግኞችን ውሃ እያጠጣን ያለነው የፈሰሰው ሃብት እንዳይባክን ለመከላከል ነው፤ ለሌሎችም አርአያ ለመሆን ነው፤ ድሬዳዋ የመዝናኛ ስፍራ እንዲኖራት ለማገዝ ጭምር ›› ብለዋል፡፡ አቶ አንተነህ አምባው የተባሉ ሰራተኛ በበኩላቸው የአስተዳደሩ ሠራተኞች ቅዳሜና እሁድ በቡድን በመደራጀት  የተተከሉትን ችግኞች ውሃ በማጠጣትና በመንከባከብ የዜግነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹እየተዝናኑ ተፈጥሮን መንከባከብ ደስ ይላል፤ በየመናፈሻው የተተከሉትን ብቻ ሳይሆን አስታዋሽ ያጡትን መንከባከብም ተገቢ ነው›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም