የልማት ማህበሩ ባዘጋጀው ቴሌቶን 130 ሚሊዮን ብር አሰባሰበ

61
ኢዜአ ታህሳስ 12 /2012 --የትግራይ ልማት ማህበር ድህነትን ለመቀነስ እያደረገ ላለው ጥረት የማህበሩ አባላትና ደጋፊዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አሳሰቡ። የልማት ማህበሩ ትናንት ባካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን 130 ሚሊዮን ብር አገኘ። በገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶኑ ላይ የተገኙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እንዳሉት፣ የልማት ማህበሩ በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና ተደራሽነትን ለማስፋት በርካታ ውጤታማ ተግባራትን አከናውኗል። በተያዘው ዓመትም ከ3 ሺህ በላይ የዳስ ትምህርት ቤቶችን ወደ ሕንጻ ክፍሎች ለመቀየር በማሰብ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ማዘጋጀቱን ተናግረዋል። ዶክተር ደብረጽዮን እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በክልሉ ካሉ በርካታ ችግሮች መካከል የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ አንዱና መሰረታዊ ጉዳይ ነው። የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ብቁና አገሩን የሚወድ ትውልድ ለማፍራት ማህበሩ የጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል። ሥራ ፈጣሪና ችግር ፈቺ ትውልድን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የትግራይ ልማት ማህበርን በገንዘብ፣ በእውቀትና በጉልበት ማጠናከር እንደሚገባም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል። በተለይ የማህበሩ አባላትና ደጋፊዎች አቅማቸውን በማሰባሰብና አንድነታቸውን በማጠናከር ለማህበሩ ሲያደርጉት የነበረውን ድጋፍ  አጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል። ከ3 ሺህ በላይ የአንደኛ ደረጃ እንዲሁም 12 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ገንብቶ ለአገልግሎት ለማብቃት እንደሚሰራ የገለጹት ድገሞ የልማት ማህበሩ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ተስፋይ ገብረእግዚአብሔር ናቸው። ለእዚህም ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈና ቀጣይነት ያለው የገንዘብ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን በትግራይ ክልል ሁሉም ዞንና ወረዳዎች እንደሚካሄድ አስታውቀዋል። የልማት ማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ የማነ በበኩላቸው፣ በቴሌቶኑ ከአንድ ቤተሰብ 1ሺህ ብር በመሰብሰብ በዳስ ውስጥ የሚማሩ 150 ሺህ ተማሪዎችን በዘመናዊ የመማሪያ ሕንጻ እንዲማሩ ለማድረግ እየተሰራ ነው። እንደ አቶ ታደሰ ገለጻ፣ ትናንት በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ላይ 130 ሚሊዮን ብር የተሰብሰብ ሲሆን፣ በቀጣይ በክልሉ ሁሉም አካባቢ በሚካሄዱ ተመሳሳይ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብሮች 1 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም