ጉባኤው በሞጣ ከተማ በሃይማኖት ተቋማት ላይ የደረሰውን ጥፋት አወገዘ

74
ኢዜአ፤ ታህሳስ 12/2012በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ በቤተ ዕምነቶች ላይ የተፈፀመውን  ተግባር እንደሚያወግዝ የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለፀ። ህዝቡ የእምነት ተቋምትን ከጥፋት ኃይሎች ነቅቶ ሊጠብቅ እንደሚገባም ጉባኤው አስታውቋል። የክልሉ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ መላከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉዓም ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በሃይማኖት ተቋማት ላይ የተፈፀመው "አስነዋሪ ጥቃት" የሚወገዝ ነው። የተፈፀመው ድርጊት "ጤነኛ አዕምሮ ያለው የሰው ልጅ ያደርገዋል ተብሎ የማይታሰብና በተንኮል የተፈፀመ ተግባር" መሆኑን ተናግረዋል። "በቤተ እምነት ተቋማቱ ላይ የተቃጣው አደጋ የሁለቱ እምነት ተከታዮች እርስ በእርስ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸውና ወደ አላስፈላጊ ግጭት እንዲገቡ ለማድረግ የተጠነሰሰ ሴራ ነው" ብለዋል። "ማንኛውም ሰው ከፈጣሪው ዘንድ በፆምና በፀሎት ፍቅርና ሰላም የሚለመንበትን ቤተእምነት ማቃጠል ምን  ያህል ከሰውነት እየወጣን ስለመምጣታችን የሚያሳይ ተግባር ነው" ሲሉም መላከ ሰላም ኤፍሬም አመልክተዋል። የሞጣ አካባቢ ህብረተሰብ ሙስሊሙ ለክርስቲያኑ፣ ክርስቲያኑ ለሙስሊሙ ለዘመናት ሲረዳዳና ሲተዛዘን አብሮ የኖረ ህዝብ መሆኑን አስታውሰው፣ ይህ አብሮነት እንዲዘልቅ የጥፋት ኃይሎችን መለየትና ለህግ እንዲቀርቡ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል። ድርጊቱን የክልሉ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በጽኑ እንደሚወግዝ ገልጸው፣ ምዕምናኑን በማረጋጋትና ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ እንዳይጓዝ በማስተማር የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል። በነገው እለትም ከፌደራልና ከክልል ቤተ እምነቶች የተውጣጣ የልዑካን ቡድን ወደሞጣ ከተማ እንደሚጓዝና ህብረተሰቡን የማረጋጋትና የማወያየት ሥራ እንደሚሰራ አመልክተዋል። መንግስትም ድርጊቱን የፈፀሙ አካላትን በመያዝና ለህግ በማቅረብ አስተማሪ የቅጣት እርምጃ እንዲወስድባቸው ጠይቀዋል። በሁለቱም ወገን የተቃጠሉ ቤተዕምነቶችን በቀጣይ ህብረተሰቡን በማሳተፍ መልሰው እንዲገነቡ የሚደረግ መሆኑን ጠቅሰው፣ "ህዝቡ ተደራጅቶ በመንቀሳቀስ የእምነት ተቋማትን ከጥፋት ኃይሎች ሊጠብቅ ይገባል" ሲሉም አሳስበዋል። የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊና የክልሉ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባል ሀጂ መሀመድ ሀሰን በበኩላቸው "የተፈጸመው ድርጊት ሁለቱንም የዕምነት ተከታዮች ያሳዘነና ያልተለመደ ነው" ብለዋል። ለዘመናት አብረው በኖሩ ህዝቦች ላይ የተፈፀመው ድርጊት "አስነዋሪና ፅንፍ የወጣ አስተሳሰብ ባላቸው አካላት"  የተፈጸመ በመሆኑ ሁለቱንም ወገኖች እንደማይወክል ተናግረዋል። "ይህ አስነዋሪና አፀያፊ ተግባር የአገራችንም ሆነ የክልላችንን ገፅታ የሚያበላሽ በመሆኑ ሁሉም ህብረተሰብ  ድርጊቱን በጋራ ሊያወግዘው ይገባል" ሲሉም ሀጂ መሀመድ አስረድተዋል። ወጣቱም ከስሜት ወጥቶ የሁለቱ ዕምነት ተከታዮች ለዘመናት በጋራ ያካበቱትን የአብሮነት እሴት በሰከነና  በሰለጠነ አግባብ በማዳበር ሊጓዝ እንደሚገባ አሳስበዋል። በሞጣ ከተማ ከትናንት በስቲያ በደረሰ የጸጥታ ችግር በአንድ ቤተክርስቲያን፣ በሦስት መስጊዶችና በንግድ ሕንጻዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም