በአበቦ ወረዳ በአንበሳ መንጋ አንድ ሰው ተበላ

79
ኢዜአ ታህሳስ 12 ቀን 2012 በጋምቤላ ክልል አበቦ ወረዳ ከዱር በወጣ የአንበሳ መንጋ አንድ ሰው መበላቱን ፖሊስ አስታወቀ። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እንደገለጸው በወረዳው በአንድ ባለሃበት እርሻ ማሳ በሥራ ላይ የነበረ ግለሰብ በአሰቃቂ ሁኔታ በአንበሳ መንጋ ተበልቷል። በኮሚሽኑ የወንጀል መካከላልና የተቋማት ጥበቃ ኃላፊ ኢንስፔክተር ጋሻው አበራ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቡ በአንበሳ መንጋ የተበላው ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት አንድ ስዓት አካባቢ ነው። ግለሰቡ  ከሌሎች ሠራተኞች ጋር በመሆን ከባለሀብቱ የእርሻ ማሳ የማሾ ሰብል በመሰብሰብ ላይ እንዳለ መንጋው ነጥሎ በመውሰድ እንደበላው ተናግረዋል። ግለሰቡ በተበላበት አካባቢ የአንበሳ መንጋ በተደጋጋሚ በቤት እንስሳትና በሰው ላይ ጉዳት ሲያደርስ እንደነበር አስታውሰዋል። እንደ ኢንስፔክተሩ ገለጻ ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ዱር እንሳሳት፣ ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመነጋገር የአንበሳ መንጋው በሰውና እንስሳት ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት የመከላከል ስራ ይሰራል። በኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጠበቃ የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሄኖክ ታምሩ አናብሰቶቹ ጉዳት እያደረሱ ያሉት ከኢንቨስትመንት እርሻ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ የአካባቢ መረበሽ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። በአካባቢው የሚገኙት አናብስቶች ቁጥር እስከ ስምንት እንደሚደረስ የገለጹት ኃላፊው "ችግሩ በፓረኩ ብቻ የሚፈታ ሳይሆን የአካባቢውን አስተዳደራዊ መዋቅር ትብብርም የሚጠይቅ ነው" ብለዋል። ጽህፈት ቤቱ ጉዳዩን ለዋና መስሪያ ቤቱ በማሳወቅ አናብስቶቹ እያደረሱ ያለውን ጉዳት መከላከል የሚቻለበት የመፍትሄ ሃሰብ እየተጠባበቀ መሆኑን አስታውቀዋል ። በወረዳው የመንደር 11 ቀቤሌ ነዋሪ አቶ ተስፋዬ ላላንጎ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት የአንበሳ መንጋው ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢው በርካታ የቀንድ ከብት፣ ፍየልና ሌሎች የቤት እንስሳትን መብላቱን ተናግረዋል። "ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከቤት እንስሳት በተጨማሪ በሰው ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው "ያሉት ነዋሪው የሚመለከተው አካል መንጋው እያደረሰ ላለው ጉዳት መፍትሄ እንዲሰጥ ጠይቀዋል። ከእዚህ በፊት በወረዳው የአንበሳ መንጋ አንድ ሰውና በርካታ የቤት እንስሳትን ስለመብላቱ ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም