በቤተ-እምነቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃትን እንደሚያወግዙ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ

77

ኢዜአ ታህሳስ 12 ቀን 2012 በቤተ-እምነቶች ላይ የሚፈጸም ማንኛውም አይነት ጥቃትን እንደሚያወግዙ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

ፕሬዚዳንቷ ይህን ያሉት አገር አቀፍ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቀን ዛሬ በሰመራ ከተማ በተከበረበት ወቅት ነው።

አገሪቱ በለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗንና በለውጥ ውስጥ የሚያልፍ አገር እንደሚያጋጥመው ሁሉ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች እየተስተዋሉ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከእዚህ በተቃራኒው ኢትዮጵያን ወደከፍታ ማማ ለማውጣት የሚያስችሉ ተስፋ ሰጪ አበረታች ጅምሮች መኖራቸውን ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል።

ለዚህም አገራችን ሰሞኑን ወደህዋ ያመጠቀችው የመረጃ መሰብሰቢያ ሳተላይት ከብዙ ተስፋ ሰጪ አመላካች ነገሮች አንዱ ማሳያ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

"የምናልማትና የምናስባት የበለጸገች አገር መገንባት የሚቻለው ህዝቦች ተከባብረውና ተፋቅረው በሰላም አብረው መኖር የሚችሉባት አገር  ስንፈጥር ነው" ብለዋል።

እንደ አገር እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን በማለፍ የሚፈለገው ደረጃ ላይ ለመድረስ ሁሉም የአገሩን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ የራሱን ሚና ሊጫወት እንደሚገባም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አስገንዝበዋል።

የተለያዩ እምነቶችና ብሔር ብሔረሰቦች ለብዙ መቶ ዓመታት በሰላምና በጋራ አብረው በኖሩባት ኢትዮጵያ በእምነትም ሆነ በብሔር ያለውን ልዩነት መሰረት በማድረግ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ተቀባይነት እንደሌላቸውም ተናግረዋል።

"በቤተ-እምነቶች ላይ የሚፈጸም ማናቸውም አይነት ጥቃት ተቀባይነት የለውም፣ የሚወገዝ ተግባርም ነው" ሲሉም ድርጊቱን አውግዘውታል።

አንድ ቡድን የሌላውን አካል መብትና ጥቅም ሲጥስ የራሱን መብትና ጥቅምንም ለመጣስ እድል እየሰጠ መሆኑ ሊታወቅ እንደሚገባ ነው ፕሬዚዳንቷ የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም