በተወሰኑ ሀይሎች የኢትዮጵያን ህዝብ ፍቅር አንድነትና ደስታ ለማደፍረስ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

137
አዲስ አበባ ሰኔ16/2010 በተወሰኑ ሀይሎች የኢትዮጵያን ህዝብ ሰላም አንድነትና ደስታ ለማደፍረስ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ላመጧቸው ለውጦች ድጋፍና እውቅና መስጠትን ዓላማ አድርጎ ዛሬ በመስቀል አደባባይ በተደረገው ሰልፍ ላይ ፍንዳታ ተከስቷል። በደረሰው ፍንዳታ ሰዎች የሞቱ ሲሆን የቆሰሉ ሰዎችም አሉ። ከፍንዳታው በኋላ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ እንዳሉት "ደስታችንና ፍቅራችንን ለማጨለም እንዲሁም አንድነታችንን ለማደፍረስ ያሰባችሁ ሃይሎች አልተሳካላችሁም" ብለዋል። ኢትዮጵያ አሁንም ለፍቅር፣ለይቅርታና ለአንድነት የዘረጋችው እጅ እንደማይታጠፍና በኢትዮጵያ ሰማይ የሚዘንበው ሰላምና ፍቅር እንደማይቀይርም ተናግረዋል። "የኢትዮጵያን ህዝብ ፍቅር አንድነትና ደስታ ለማደፍረስ ያሳባችሁ ሃይሎች ትናትም አልተሳካላችሁም ዛሬም አልተሳካላችሁም ነገም አይሳካላችሁም" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ። ይሄን ያደረጋችሁ ሃይሎች ከእኩይ ተግባራችሁ በመመለስ መንግስትና ህዝብ ወዳልተገባ አቅጣጫ እንዳይሄዱ ጥንቃቄ ማድረግና መታረም ቢቻል መልካም እንደሆነ አመልክተዋል። ዛሬ የተከፈለው መስዋዕትነት ለኢትዮጵያ አንድነት፣ሰላምና ፍቅር የተከፈለ ነው ሲሉ ገልጸውታል። "ኢትዮጵያን ከጀመረችው የፍቅርና የይቅርታ መንገድ ሊገታት የሚችል ሃይል እንደሌለና በተሸነፈና በወደቀ ሀሳብ አንቆምም" ብለዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረው ልበ ሰፊነት፣አንድነትና ጠንካራነት እንዲሁም የመደመር እሳቤ በትንሽ ክስተት በፍጹም ወደ ኋላ መመለስ እንደሌለበት ተናግረዋል። በሰልፉ ምክንያት ህይወታቸውን መስዋዕት ላደረጉ ዜጎች ቤተሰቦች መጽናናትን እንዲሰጣቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተመኝተዋል። ዛሬ የሞቱ ሰዎች ቤተሰቦቻቸው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው የኔም ወንድሞች የሁሉም ወንድሞች በደምና በኢትዮጵያዊነት የሁሉም እህትና ወንድም ናቸው ብለዋል ዶክተር አብይ አህመድ። በጉዳዩ ዙሪያ ፖሊስ ዝርዝር ምርመራ እያካሄደ መሆኑንና ጥናቱ ሲጠናቀቅ በይፋ እንደሚገለጽና በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ያዩትንና የሰሙትን  ለፖሊስ እንዲያሳውቁ አሳስበዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም