በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲካሄድ የቆየው የአትሌቲክስ ውድድር በመከላከያ ክለብ የበላይነት ተጠናቀቀ

60

ኢዜአ ታህሳስ 12 ቀን 2012 የኢትዮጵያ የአጭር፣ የመካከለኛ፣ የሶስት ሺህ ሜትር መሰናክል፣ የእርምጃና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመከላከያ ክለብ የበላይነ ዛሬ ተጠናቀቀ።

ባለፉት ስድስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲካሄድ የቆየው ይህ ውድድር ዛሬ በማጠናቀቂያ እለት የ1 ሺህ 500 ሜትርና 200 ሜትር ወንዶችና ሴቶች፣ በወንዶች ከፍታ ዝላይ የፍጻሜ ውድድሮች ተካሂደዋል።

በወንዶች የ1 ሺህ 500 ሜትር ውድድር  አትሌት ታደሰ ለሚ ከኦሮሚያ ውሃ ስራዎች ውድድሩን በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ አትሌት መልካሙ ዘገየ ከጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ሁለተኛ ወገኔ አዲሱ ከሀዋሳ ከተማ ሶስተኛ ሆነው ጨርሰዋል።

ለተመልካች አዝናኝ በነበረው የከፍታ ዝላይ የሲዳማ ቡናው አትሌት ዲፕ ሊም 2 ሜትር ከ10 ሴንቲ ሜትር በመዝለል አሸናፊ ሆኗል። አትሌት ኡጁሉ አንበሴ ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሁለተኛ፤ ስቴቨን ያዋል ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሶስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቀዋል።

በውድድሩ ማጠናቀቂያ የወንዶችና ሴቶች የዱላ ቅብብልን ጨምሮ ሌሎች የፍጻሜ ውድድሮችም ተካሂደዋል።

የዛሬውን ጨምሮ ባለፉት ስድስት ቀናት በተካሄደው በዚህ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በወንዶች አጠቃላይ አሸናፊ መከላከያ ሆኖ አጠናቋል።

እንዲሁም ሲዳማ ቡና ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቀቅ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግም ሶስተኛ ደረጃን ማግኘት ችሏል።

በሴቶች መካከል በተደረገው ውድድርም መከላከያና ሲዳማ ቡና አንደኛና ሁለተኛ ሆነው ሲያጠናቅቁ ሀዋሳ ከተማ ሶስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቀዋል።

በዚህ ሻምፒዮና በሴቶችና ወንዶች አጠቃላይ ውጤት መሰረት  የተሻለ ነጥብ በመሰብሰብ መከላከያ ቀዳሚ ሆኖ በማጠናቀቁ የዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችሏል።

እንዲሁም ሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ እንደየ ቅደም ተከተላቸው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም