ብልጽግና ፓርቲ በኢህአዴግ አደረጃጀት የነበረውን ድክመት ካስወገደ አገራዊ አንድነት፣ ሰላምና ልማትን የመፍጠር እድል አለው-ምሁራን

87

ኢዜአ ታህሳስ 11/2012 አዲስ የተመሰረተው ብልጽግና ፓርቲ በኢህአዴግ አደረጃጀት የነበረውን ድክመት ማስወገድ ከቻለ አገራዊ አንድነትን፣ ሰላምንና ልማትን የመፍጠር ዕድል ይኖረዋል ሲሉ ምሁራን ተናገሩ።

በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ፖለቲካ ሁናቴና የኢህአዴግ ወደ ብልጽግና ፓርቲ ሽግግርን አስመልክቶ ምሁራንን ያሳተፈ የውይይት መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። "መቃ ፕሮሞሽን" በተሰኘ ድርጅት አዘጋጅነት በተካሄደው ውይይት ላይ የተሳተፉት ምሁራን የኢህአዴግ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ አገር የመምራት ጉዞ ፍትሃዊነት የጎደለው፣ አካታችነት የሌለውና ኢ-ዴሞክራሲያዊ እንደነበር ተናግረዋል።

ኢህአዴግ ምሁራንንና አርብቶ አደር አካባቢን ያገለለ ርዕዮተ ዓለም የሚከተል፣ የጋራ አገራዊ እሴቶችንና አገራዊ አንድነትን የዘነጋ እንዲሁም የሚያራምደው ፌዴራሊዝም የይምሰል እንደነበር ነው ምሁራኑ በውይይቱ ላይ ያነሱት።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ታደሰ ጃለታ እንደሚሉት የኢህአዴግ የግንባርነት አደረጃጀት አንድ የኢኮኖሚ ፖለቲካ-ማኅበረሰብ ከመፍጠር በተቃራኒ ሆነ ተብሎ የጋራ እሴቶች እንዳይጎሉ የተደረበት ነበር።

በዚህ አደረጃጀች ችግርና ህዝባዊ ጥያቄዎች በመጨረሻም አገር መምራት ከማይችልበት ደረጃ ደርሶ ለውጥ እንዲያደርግ ማስገደዱን ያነሳሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህር የሆኑት ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ በበኩላቸው የኢህአዴግ የግንባርነት ጉዞ በፖለቲካ፣ በሃይማኖት፣ በባህል ረገድ በሊሂቃን መካከል ከመናበብ ይልቅ እየተጓተቱ የአገርን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ ችግር መፍጠሩን ይገልጻሉ።

የኢህአዴግ ማኅበራዊ አወቃቀር አንዱን ጠላት፣ ሌላውን ወዳጅ አድርጎ የሚፈርጅ መደብ የነበረበት፣ ከአገራዊ አንድነት ይልቅ ብሔራዊ ማንነት ላይ ብቻ ያተኮረ እንደነበር ያወሳሉ።

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የራያ ማንነት ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ደሳለኝ ፌዴራሊዝም ስርዓት ዓላማ ህዝቦች ተፈቃቅደው እምቅ ሃብታቸውን ለመፍጠር፣ ራስን በራስ ለማስተዳደር፣ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ ነው ባይ ናቸው።

ላለፉት ዓመታት የነበረው ፌዴራሊዝም ግን መጥፎውን ትርክት በማጉላትና የጋራ የሆኑ እሴቶችን በማጥፋት አገራዊ አንድነት እንዳይፈጠር የተደረገበት፣ እንደ ራያ ያሉ ህዝቦችም የማንነት ጥያቄ የተጨፈለቀበት መሆኑን ይገልጻሉ።

ምሁራኑ እንደሚሉት አገራዊ ለውጥ መምጣቱ፣ ኢህአዴግም ወደ ብልጽግና ፓርቲ መሸጋገሩ አማራጭ ያልነበረው ሂደት መሆኑን ተናግረዋል።

ከዲላ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶክተር ይሁኔ አየለ አንዱ ችግር የስርዓተ ትምህርቱ ጽንሰ ሃሳብ ከውጭ ብቻ መቀዳቱ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን በብልጽግና ፓርቲ የተጀመረው አገር በቀል የመደመር እሳቤ መኖሩን ይደግፋሉ።

በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ምርምር የሚያደርጉት ዶክተር ወሰን ባዩም ውህደቱ በፓርቲዎች ውስጥ መተማመንን የሚፈጥር፣ ለተፎካካሪዎችም ምሳሌ የሚሆን መሆኑን ይገልጻሉ።

በአጠቃላይ ውህዱ የብልጽግና ፓርቲ በኢህአዴግ የታዩ አደረጃጀት ችግሮችን ማስወገድ ከቻለ አገራዊ አንድነትን፣ ሰላምና ልማትን የመፍጠር ዕድል ይኖረዋል ሲሉ ምሁራኑ ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ፓርቲው ወደ ውህደት መምጣቱ ከአምባገነናዊነት ወደ ዴሞክራሲዊነት፣ እኩልነት፣ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወደእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ ከማስመሰል ፌዴራሊዝም ወደእውነተኛ ሕብረ ብሔራዊነትና ብዝሃነት፣ ከዘውጌነት ወደአገራዊ አንድነት ለማመጣት የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም