የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን በሰላምና መፍትሄ አምጭ የጋዜጠኝነት ፍልስፍና ቢቃኙ ውጤት ማምጣት ይቻላል

78
ኢዜአ ታህሳስ  11 /2012  የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን በሰላምና መፍትሄ አምጭ የጋዜጠኝነት ፍልስፍና ቢቃኙ በአገሪቱ አንድነት፣ሰላምና ልማት ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል በቻይና ኮሙኒኬሽን ዩኒቨርስቲ የአፍሪካ ኮሙኒኬሽን ምርምር ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ዣንግ ዩንኩይ አስታወቁ። ዳይሬክተሯ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በኢትዮጵያ ያለው የመገናኛ ብዙሃን አሰራር ብዙ ክፍተቶች እንደሚታዩበት መረዳታቸውን ገልፀዋል። በኢትዮጵያ ባደረጉት ቆይታ ከተለያዩ የግልና የህዝብ መገናኛ ብዙሃን ከተውጣጡ ጋዜጠኞች ጋር መነጋገራቸውን አንስተዋል። በዚህም የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን እንደ አገር አንድ የሚያደርጋቸው አገራዊና ህዝባዊ መሰረት ያለው አጀንዳ እንደሌላቸው መገንዘባቸውን ጠቅሰዋል። ይልቁንም ሚዲያዎቹ ሁለት ፅንፍ የወጡ አጀንዳዎችን የሚያራምዱ ሆነው ማግኘታቸውንም አስረድተዋል። ሆኖም በተለይ የአሁኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ የህዝብና የአገርን ጥቅም መሰረት ያደረገ አንድ የጋራ አጀንዳ ያላቸው የሚዲያ ተቋማትን የጋራ ጥረት ይጠይቃል ብለዋል። በመሆኑም ሚዲያዎቹ ይህንን እውን በማድረግ ሙያዊ ግዴታቸውን ቢወጡ ትልቅ ውጤት ማምጣት ይችላሉ ሲሉም ተናግረዋል። በዚህ ረገድ በተለይ የሰላምና መፍትሄ አምጭ ጋዜጠኝነት ዓይነተኛው መሳሪያ መሆኑን በመጥቀስ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቻይናዊያንና ምዕራባዊያን ስራ ላይ የዋለው የመፍትሄ ተኮር ጋዜጠኝነት /Constructive Journalism/ ጥሩ ውጤት እያመጣ ያለና በኢትዮጵያም ቢተገበር ውጤታማ የሚሆን ነው ብለዋል። ይህ የመፍትሄ ተኮር የጋዜጠኝነት ፍልስፍና ከሰላምና ከልማታዊ ጋዜጠኝነት ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑም እንዲሁ። ይሁን እንጂ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በኢትዮጵያ በዘርፉ ተከታታይ ስልጠና እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። መንግስትና የትምህር ተቋማትም ለዘርፉ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባም አክለዋል። የቻይናው የኮሙኒኬሽን ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያን የመገናኛ ብዙሃን ኢንዱስትሪ ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍም ገልፀዋል። "በቀጣይም ስልጠና በመስጠት፣ የመገናኛ ብዙሃን ኮንፍረንስ በማዘጋጀት እንዲሁም ሙያውን ለመደገፍ የሚያስፈልጉ የገንዘብ ድጋፎችን ከማፈላለግ አኳያ ድጋፍ እናደርጋለን" ብለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም